የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሐፍት  ኤጀንሲ ከደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከጋሞ ጎፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ‹‹ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል›› በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 30 - ሚያዝያ 3/2009 ዓም የቆየ ዓውደ ርዕይ በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የንባብ ባህልን ያዳበረ ማህበረሰብ መፍጠርና ወጣቱ ትውልድ የፈጠራ ክህሎቱን በማሳደግ ለሀገሩ የህዳሴ ጉዞ  በትጋት እንዲሠራ ግንዛቤ ማስጨበጥ የአውደ ርዕዩ ዓላማ መሆኑን በብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሐፍት ኤጀንሲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አዘዘ ጌትነት ተናግረዋል፡፡

የወጣቱ የንባብ ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆን ለአውደ ርዕዩ መዘጋጀት ምክንያት እንደሆነ የገለፁት አቶ አዘዘ ወጣቱ የትምህርት ደረጃን ለማሻሻል ብቻ ከማንበብ ባሻገር ንባብን እንደ ጥሩ ባህል ቆጥሮ ሣይንስና ቴክኖሎጂን ለማላመድ እንዲሁም ችግር ፈቺ ምርምር ለመሥራት ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑ ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ፕሮግራም ላይ እንደተገለፀው ወላጆች ለህፃናት ንባብ የሚሰጡት ትኩረት ማነስ፣ የመጽሐፍት የአንባቢውን የመግዛት አቅም ያላገናዘቡ መሆን፣ በክልልም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በበቂ ሁኔታ የተደራጁ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሐፍት አለመኖራቸው፣ ምሁራንና የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም መሰል ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ እድገት ትኩረት ሰጥተው አለመሥራታቸው የንባብ ባህሉ እንዳይዳብር ማነቆ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ አቡቶ አኒቶ እንደገለጹት በክልሉ ከ532 ያላነሱ ቤተ-መጽሐፍት በቀበሌና በት/ቤት ደረጃ ቢኖሩም ከተገልጋዩ ህብረተሰብ አንፃር ተደራሽነታቸው አናሳ ነው፡፡ ክልሉ ጅምር እንቅስቃሴዎቹን አጠናክሮ እንዲቀጥልና የንባብ ባህልን ያዳበረ ማህበረሰብ ለመፍጠር ደራሲያን፣ መምህራን፣ ወላጆች፣ የመገናኛ ብዙሃንና ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡

‹አንባቢ ትውልድ ሲኖር ማመዛዘን ይኖራል፤ ግምቶች ቀርተው እውቀት በመረጃ የተደገፈ ይሆናል፡፡›› ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ የፍሬው መጽሐፍት መደብር ባለቤት አቶ ፍሬው አሰፋ የንባብ ባህልን ከጅምሩ ኮትኩቶ ለማሳደግ ህፃናት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያገናዘበ የመጽሐፍ ዋጋ መኖር የንባብ ባህልን ለማሳደግ እንደሚረዳም ጠቁመዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ የትነበርሽ ሙሉ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ በረከት በቀለ በበኩሉ ማንበብ ሙሉ ሰው የሚያደርገው አንባቢው በንባብ ውስጥ ያለውን ምስጢር ሲረዳ በመሆኑ ወላጆች ለልጆቻቸው መጽሐፍትን ገዝተው ከመስጠት ባሻገር የመከታተል ልማድን ሊያዳብሩ ይገባል ብሏል፡፡

ጥንታዊ የብራና ጽሑፎች፣ ቆየት ያሉ የፍርድ ቤት መዝገቦች፣ በግዕዝ ቋንቋ የተፃፉ የነገስታት ታሪኮች፣ የተለያዩ መጽሐፍት፣ ፎቶግራፎችና መሠል ሥራዎች በአውደ ርዕዩ ከቀረቡት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡