ዩኒቨርሲቲው በፎረንሲክ ኬሚስትሪና ቶክሲኮሎጂ የመጀመሪያውን ሀገር አቀፍ ዓውደ ጥናት ሚያዝያ 21/2009 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ህክምና ኮሌጅ፣ ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታልና መቐለ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችለው የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረምም በፎረንሲክ ሣይንስ ዘርፍ አሻራውን ለማስቀመጥ አንድ እርምጃ ተጉዟል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ተቋማቱ በፎረንሲክ ሣይንስ የደረሱበትን የእውቀት፣ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ደረጃ፣ የሰው ኃይል እንዲሁም ልምድና ተሞክሮ እንዲጋሩ እና በትምህርትና ስልጠና ተቀናጅተው እንዲሠሩ የመግባቢያ ሰነዱ መሠረት የሚጥል መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ኃላፊና የዓውደ ጥናቱ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አብዩ ኬሬቦ ተናግረዋል፡፡ ለቅድመ ምረቃና ድህረ ምረቃ ተማሪዎች ጥናትና ምርምሮቻቸውን በተሻለ አቅም እንዲያከናውኑ ዕድል የሚፈጥርና ህብረተሰቡ ከሣይንሱ ጋር ያለውን ቁርኝት የሚያጠናክርም ነው ብለዋል፡፡

‹‹ወንጀል ድንበር የማይበግረው እንደመሆኑ ብሔራዊ ትኩረትና ተቋማዊ ትብብር ወሳኝ ነው›› ያሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዓውደ ጥናቱ ተፈላጊውን ውጤት ለማምጣት ተቋማት ኅብረታቸውን የሚያጠናክሩበት እንዲሁም የዘርፉን ችግሮችና መልካም አጋጣሚዎች የሚፈትሹበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የፎረንሲክ ሣይንስ ምንነት፣ በሀገራችን የደረሰበት ደረጃ፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችና መፍትሔዎቻቸው እንዲሁም አጋር ተቋማቱ በዘርፉ ያላቸው ልምድና ተሞክሮ ላይ በስፋት ውይይት ተደርጓል፡፡ ባለንበት የቴክኖሎጂ ዘመን የወንጀል ምርመራ የሰለጠነ ባለሙያ፣ ረቂቅ ስልትና ተኣማኒ ማስረጃዎችን የሚጠይቅ ሲሆን ፎረንሲክ ሣይንስ የወንጀል ማስረጃዎችን በሣይንሳዊ ዘዴ ለመመርመር ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ ፎረንሲክ ቶክሲኮሎጂ መርዛማ ንጥረ ነገሮች፣ አደንዛዥ ዕፆችንና ኬሚካሎች በሰው ሰውነት ላይ የሚስከትሉትን ጉዳት በማጥናት የሞት ምክንያቶችን ለመተንተን የሚያስችል ሣይንስ ነው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፎረንሲክ ኬሚስትሪና ቶክሲኮሎጂ የትምህርት ፕሮግራምን በማጠናከር ተማሪዎች በተግባር ትምህርት ታግዘው ብቁ እንዲሆኑና የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በማፍራት ወንጀልና ወንጀል ነክ ጉዳዮችን ለመከላከል በማለም የዘመናዊ መሣሪያዎች ተከላ ማካሄዱ ይታወሳል፡፡ መሣሪያዎቹ በ11 ሚሊየን ብር ከእንግሊዝ ሀገር የገቡ ሲሆን አሻራ፣ ፈሳሽ ነገሮች፣ የተጭበረበሩ ዶክመንቶች፣ የባንክ ኖቶች፣ ፓስፖርት፣ የእጅ ፅሁፍ አሻራዎችና ያረጁ ወረቀቶች ላይ ያሉ ጽሑፎችን ለመመርመር የሚያስችሉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት አቶ አየለ ሙሉጌታ እንደገለፁት የፎረንሲክ ሣይንስ ቴክኒካዊ ምርመራን በማጠናከር የወንጀል ምርመራ ዘዴ ታክቲካዊ ብቻ እንዳይሆን ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ቢሆንም በሀገራችን በተለያዩ ምክንያቶች ዘርፉ በርካታ ክፍተቶች ያሉበት ነው፡፡ የፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ ዳይሬክቶሬት ዘመናዊ የምርመራ መሣሪያዎች  ቢኖሩትም በሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ምክንያት የተወሱ መሣሪያዎች ግልጋሎት እየሰጡ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል በመሣሪያ አለመኖር ምክንያት አንዳንድ ወሳኝ ምርመራዎችን በተቋሙ ለማድረግ አልተቻለም፡፡ ለአብነትም የዲኤንኤ ምርመራ ናሙናዎችን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሣይንስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አማኑኤል ኃይሌ ‹‹በሀገራችን እምብዛም ያልተለመደ ጽንሰ ሀሣብ››  ባሉት የፎረንሲክ ህክምና ላይ የዩኒቨርሲቲያቸውን ልምድ ጠቅሰው ሲያብራሩ በህክምና ባለሙያዎችና ቁሳቁሶች እጥረት እንዲሁም በቂ ትኩረት ባለማግኘቱ ዘርፉ በሀገሪቱ የፍትህ ሥርዓት የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ እንዳያበረክት ሆኗል ብለዋል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሀገሪቱ በፈጣን ዕድገትና ለውጥ ላይ መገኘቷ ዜጎች ከጤናና የፍትህ መስኮች የተሻለ ግልጋሎት እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል፡፡ ያለ ፎረንሲክ ሣይንስ ደግሞ የተሻለ የፍትህ ሥርዓትን መጠበቅ የማይታለም መሆኑን በማመን መቐለ ዩኒቨርሲቲ ከአራት ዓመታት በፊት የፎረንሲክ ህክምናን በመጀመር የዕድሜ፣ የፆታዊ ትንኮሳና የአስከሬን ምርመራ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከዚህም ባሻገር ዩኒቨርሲቲው የፎረንሲክ ህክምና ስፔሻላይዜሽን ፕሮግራሙን ከ3 ዓመታት በፊት የከፈተ ሲሆን በ8 ወራት ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያውን ባች ያስመርቃል፡፡

‹‹በርካታ የፎረንሲክ በተለይም ከምረዛና የአደንዛዥ ዕፅ ጋር የተያያዙ የወንጀል ምርመራዎች መቋጫ ሳይበጅላቸው በእንጥልጥል ይቀራሉ፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በፎረንሲክ ኬሚስትሪና ቶክሲኮሎጂ የከፈተው የትምህርት ፕሮግራም ብሎም በጋራ ለመሥራት መሠረት መጣላችን መሰል ክፍተቶችን እንደሚሞላ ተስፋ አለኝ፡፡ ዓውደ ጥናቱም ዩኒቨርሲቲው፣ ተማሪዎቹና አጋር ተቋማት በፎረንሲክ ሣይንስ ዘርፍ ለሚጠብቃቸው የጋራ ሥራ በር ከፋች ነው፡፡›› ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡

2ኛውን ዙር ሀገር ዓቀፍ ዓውደ ጥናት ለማዘጋጀት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተራውን ወስዷል፡፡