የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ከማኔጅመንት እና ሥነ-ባህርይ ትምህርት ክፍሎች ጋር በመተባበር ለሴት መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ‹‹የአመራር ክህሎትና የውሳኔ ሰጪነት ሚና›› በሚል ርዕስ ከሚያዝያ 3-4/2009 ዓ.ም የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የሥልጠናው ዓላማ የሴቶችን ተሳትፎና የአመራር አቅም በየዘርፉ በማሳደግ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ ሆነው ባላቸው የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ብቃት በአመራር ቦታዎች መሥራት እንዲችሉ አቅም መፍጠር መሆኑን የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ታደለ ሸዋ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው በተለያዩ የአመራር ቦታዎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማረጋገጥ በየዘርፉ የአመራር አቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በየደረጃው የሴት አመራሮች ቁጥር ከቀድሞው ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ቢሆንም ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው አቅጣጫ በስትራቴጅክ ዕቅድ የተያዘ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ውጤታማ የአመራር ፅንሰ ሃሳብ፣ የአሠራር ሥርዓት፣ ባህሪያትና መገለጫዎች እንዲሁም የውሳኔ አሰጣጥ ዓይነቶችና ሂደቶች የሚሉ ርዕሶች በሥልጠናው ተዳሰዋል፡፡ ሴቶች በራስ የመተማመንና ውሳኔ የመስጠት አቅማቸው የተሻለ ሆኖ ሳለ በተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊና ባህላዊ ተፅዕኖዎች ምክንያት አቅማቸውን በአግባቡ እየተጠቀሙ አይደለም፡፡ ተጽዕኖዎቹን ተቋቁሞ ስኬታማ ለመሆን ሴቶች መልካም አርአያዎችን መመልከት፣ ዕውቀታቸውን ለማሳደግ መጣርና የይቻላል መንፈስን ማዳበር እንደሚገባቸው በሥልጠናው ተብራርቷል፡፡

በሥልጠናው የሁሉም ካምፓሶች ሴት መምህራንና የአስተዳደር ሠርተኞች የተሳተፉ ሲሆን ሠልጣኞቹ የሥነ-ልቦና ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችላቸውን ግንዛቤ መጨበጣቸውን ተናግረዋል፡፡