የ2009 በጀት ዓመት የ9 ወራት የሥራ ክንውን ሪፖርት ግምገማ ተካሄደ

የዩኒቨርሲቲው የ2009 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች፣ የት/ት ክፍል ኃላፊዎችና የቡድን መሪዎች በተገኙበት ሚያዝያ 5/2009 ዓ.ም ቀርቦ ግምገማ ተካሂዶበታል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የተከናወኑ ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮች፣ የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎችና ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን የስትራቴጂክ ዕ/ዝ/ክ/ግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዝሙ ቀልቦ በገለፃና በሰንጠረዥ አቅርበዋል፡፡ በሪፖርቱ እንደተገለፀው የኦሞ ዓለም አቀፍ ሣይንስ ጆርናል የመጀመሪያ ዕትም መሠራጨቱ፣ ለምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች ቤልጂየም ሀገር ከሚገኙ አምስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የልማት ትብብር በይፋ መጀመሩ በዚህም 17 የፒ ኤች ዲ ትምህርት ዕጩዎችን ለመላክ ምልመላ መጠናቀቁ፣ ከሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት 1.7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መገኘቱ እንዲሁም 4ኛው ዙር የሥነ-ህንፃና ከተማ ንድፍ 46 ተማሪዎች መመረቃቸው ከተከናወኑ ዓበይት ተግባራት መካከል ተጠቅሰዋል፡፡

ቀደም ሲል ይታይ የነበረው የግንባታ ሥራ መጓተት የቅርብ ክትትልን በማጠናከር መሻሻል የታየበት ሲሆን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግርን ለመቅረፍ አዳዲስ ጀኔሬተሮች ተገዝተው ሥራ ጀምረዋል፡፡ አዳዲስ የኔትወርክ መስመሮችን በመዘርጋትም የኢንተርኔት መቆራረጥ ችግርን መቅረፍ መቻሉ ተገልጿል፡፡

በአንፃሩ ዩኒቨርሲቲው የራሱ የሆነ ማስተማሪያ ሆስፒታል የሌለው በመሆኑ ለከፍተኛ ወጪ መዳረጉ፣ በፋይናንስ ሥራ ክፍሎች የባለሙያ እጥረት መኖሩና አማካሪ ተቋራጭ ድርጅቶች የተሟላ ዲዛይን በወቅቱ አለማቅረባቸው ካጋጠሙ ችግሮች መካከል ለአብነት ተነስተዋል፡፡

የትምህርት ጥራትና የመልካም አስተዳደር ውይይቶችን እንደ ግብዓት በመውሰድ ከተማሪዎች፣ ከመምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ጋር የተያያዙ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመለየት መሥራትና የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊትን ማጠናከር በቀጣይ የዕቅድ ትግበራ ጊዜያት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ በበጀት ዓመቱ የታዩ ክፍተቶችን በመሙላት በርካታ የላቁ አፈፃፀሞችን ለማስመዝገብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አፅንኦት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡