ዩኒቨርሲቲው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 20 ሚሊየን ብር አበረከተ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልል የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ሲዘዋወር ቆይቶ የጋሞ ጎፋ ዞን የመጨረሻ ጉዞውን በማጠናቀቅ ግንቦት 09/2009 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ከተማ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው ልዩ የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት ለግድቡ ግንባታ 20 ሚሊየን ብር ስጦታ ማበርከቱን አስታውቋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ‹‹የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የተቀበለው የታላቁ የህዳሴ ግድብ መታሰቢያ ዋንጫ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ የምናስቀጥልበትን ተሳትፎ የሚያሳይ ነው›› ብለዋል። የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዩኒቨርሲቲው በቦንድ ግዢና በሌሎችም ድጋፎች አስተዋጽኦውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የጋሞ ጋፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚጫወተው ሚና  ባሻገር በዞኑ የሚካሄዱ የልማት እንቅስቃሴዎችን በሙያና በፋይናስ በመደገፍ ረገድ የመሪነት ድርሻ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለህዳሴው ግድብ ዋንጫ አቀባበል ያበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ ለዚህ ማሳያ በመሆኑ ለተደረገው ድጋፍ በዞኑ መንግሥትና ህዝብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ለዞኑ ልማት መሰል ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ የዩኒቨርሲቲው፣ የዞኑ፣ የዙሪያ ወረዳዎችና የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም የከተማውና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ተገኝተዋል፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረ እስካሁን የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ሁለት ዙር ቦንድ ግዢ የፈፀመ ሲሆን ሦስተኛውን ዙር የቦንድ ግዢ ለመፈፀም ቃል ገብቷል፡፡