የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ከኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ጋር በመተባበር በኢንደስትሪ አስተዳዳር፣ በጥራት ቁጥጥርና አስተዳደር፣ በሥራ ፈጠራ ምንነትና ራስን በማዘጋጀት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃን በጠበቀ መልኩ የኢንደስትሪ ቤተ-ሙከራ አስተዳደርን በተመለከተ ለኢንደስትሪያል ኬሚስትሪ ተመራቂ ተማሪዎች ከግንቦት 11-12/2009 ዓ/ም ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር አብዩ ኬሬቦ እንደገለፁት ስልጠናው ተመራቂ ተማሪዎቹ በኢንደስትሪ አስተዳደር፣ በኢንደስትሪ ቤተ-ሙከራ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ  ፅንሰ-ሃሳብና በሥራ ፈጠራ ምንነት ላይ ግንዛቤ ጨብጠው በዘርፉ ሲሰማሩ የሚገጥሟቸውን ፈተናዎችን በቀላሉ በማለፍ ተወዳዳሪ ባለሙያዎች እንዲሆኑ ያስችላል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በበኩላቸው ሀገራችን ወደ ኢንደስትሪ በምታደርገው ሽግግርና ከሀገሪቱ የሰው ኃይል ፍላጎት አኳያ ሠልጣኝ ተማሪዎች ከወረቀት የዘለለ እውቀት ጨብጠው ከመንግስት ሥራ ጠባቂነት አስተሳሰብ በመላቀቅ ሥራ የመፍጠር ባህልን ሊያዳብሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ዘባሲል ጣሰው እና የአዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ አሸናፊ ታዬ ስልጠናውን ሲሰጡ እንደተናገሩት ሠልጣኞች ኢንደስትሪው የሚጠይቀውን ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ (አይኤስኦ) ተግባራዊ በማድረግ የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከቴክኖሎጂው እኩል ሊጓዙ ይገባል፡፡ በተጨማሪም በማህበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት የሥራ ፈጠራ እውቀታቸውን ወደ ገንዘብ የሚቀይሩበትን ሣይንሳዊ መንገድ መጠቀም ይችላሉ፡፡

ሠልጣኞች በአስተያየታቸው እንደገለፁት ስልጠናው በኢንደስትሪው ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ከማዳበሩም በተጨማሪ ወደ ሥራ ዓለም ከመግባታቸው በፊት የተሻሉ አማራጮችን እንዲከተሉ፣ የሥራ ፈጠራ ክህሎታቸው እንዲጨምርና ሀገሪቱ በቴክኖሎጂው ዘርፍ በምታደርገው የልማት ውድድር ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡

በስልጠናው 50 የኢንደስትሪያል ኬሚስትሪ ተመራቂ ተማሪዎችና የትምህርት ክፍሉ አስተባባሪዎች የተካፈሉ ሲሆን በስልጠናው መጨረሻ የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡