ቡድኑ የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርግም ወደ ቀጣዮቹ 16 ቡድኖች ሳይቀላቀል ቀርቷል

የዩኒቨርሲቲው የወንዶች እግር ኳስ ቡድን የደ/ብ/ብ/ህ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከግንቦት 12-27/09/2009 ዓ/ም በሀላባ ከተማ ባዘጋጀው የክልሉ እግር ኳስ ሻምፒዮና ላይ በመሳተፍ የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያደርግም ወደ ቀጣዩቹ 16 ቡድኖች ሳይቀላቀል ቀርቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

ቡድኑ በማጣሪያ ጨዋታ ከጉራጌው መስቃን ወረዳ 2ለ2 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያይ ከሀዋሳው ንዋይ ላቦራቶሪ ቡድን ጋር ባደረገው 2ኛ ጨዋታ 1ለ0 ተረቷል፡፡ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከስልጤው ዳሎቻ ወረዳ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ ሲጠበቅበት በ2ለ2 አቻ ውጤት በመለያየቱና በተመሳሳይ ሰዓት የሀዋሳው ንዋይ ላቦራቶሪ ቡድን ከጉራጌው መስቃን ወረዳ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ በንዋይ ላቦራቶሪ ቡድን አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ ቢጠበቅም 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት በመጠናቀቁ የዩኒቨርሲቲው ቡድን ወደ ቀጣዩ ዙር ሳያልፍ ቀርቷል፡፡

የቡድኑ አመራሮች በቂ የውይይት መድረክ አለማመቻቸታቸው፣ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች አለመደረጋቸው፣ የቅንጅት ችግሮችና ተጫዋቾች ያገኟቸውን የጎል እድሎች አለመጠቀማቸው ለውጤት ማጣት ምክንያቶች መሆናቸውን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው የወንዶች እግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝና የስፖርት ሣይንስ መምህር አቶ አይቸው አበበ ለቀጣዩ ውድድር ከክፍተቶቹ በመማር የተሻለ ልንሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

የስፖርት አካዳሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ቾምቤ አናጋው በበኩላቸው ምንም እንኳን ቡድኑ በነበሩበት የቅንጅትና መሠል ችግሮች ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ባይችልም በቀጣዩ የ2010 በጀት ዓመት ወደ ብሄራዊ ሊግ ለመግባት አስፈላጊውን የትጥቅና ሌሎች ግብዓቶች አሟልቶ ቡድኑን በተሻለ ሁኔታ ለማደራጀት አካዳሚው ከወዲሁ የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተጫዋች ልዩታሪክ አሻግሬ ‹‹አቅማችንን ሊያሳይ በሚችል ሁኔታ ጥሩ ጨዋታ ለማሳየት ብንሞክርም ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ያደረግነው የልምምድ ጨዋታና የቅንጅት ማነስ ለሽንፈታችን ምክንያቶች ነበሩ›› ብሏል፡፡