4ኛው ‹‹ሣይንስ ለዘላቂ ልማት›› ሀገር አቀፍ ዓውደ ጥናት ተካሄደ

ዩኒቨርሲቲው 4ኛውን ‹‹ሣይንስ ለዘላቂ ልማት›› ሀገር አቀፍ ዓውደ ጥናት ከግንቦት 4-5/2009 ዓ.ም አካሂዷል፡፡

በዓውደ ጥናቱ በግብርና ሣይንስ፣ በህክምናና ጤና እንዲሁም በተፈጥሮ ሣይንስ ዘርፎች 36 የምርምር ሥራዎች ቀርበዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ዓውደ ጥናቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች የሀሳብ ልውውጥ እንዲያደርጉ፣ ዩኒቨርሲቲዎች እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት በተለያዩ መስኮች እንዲያጠናክሩ እንዲሁም ሣይንስ ለዘላቂ ልማት የሚጫወተውን ሚና አጉልቶ ለማሳየት የሚረዳ መሆኑን የምር/ዳይ/ዳይሬክተር ዶ/ር ስምኦን ሽብሩ ተናግረዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ በምርትና ምርታማነት እና በጤና ላይ ያለው ተፅዕኖ፣ የእንስሳት ምርትና ምርታማነት ለባዮቴክኖሎጂ ያለው ሚና፣ የሌሽማኒያሲስ በሽታ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ የማዳበሪያ አጠቃቀም ለምርታማነት ያለው ጠቀሜታ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በህፃናት ላይ የሚያስከትለው የጤና መታወክ እንዲሁም ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም  በዓውደ ጥናቱ ከቀረቡ የምርምር ሥራዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለፁት የምርምር ሥራዎች ያልተዳሰሱ፣ የዩኒቨርሲቲውን የትኩረት አቅጣጫዎች መሠረት ያደረጉና በቀዳሚነት የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ መሆን ያለባቸው ሲሆን በየዘርፉ ያሉ ተመራማሪዎችም ሊበረታቱና ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

የዓለም ዓቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ዶ/ር አዛገ ተገኝ በበኩላቸው ሀገራችን በእንስሳት ሀብቷ ከአፍሪካ በቀዳሚነት የምትታወቅ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው ነገር ግን በአቅርቦትና አጠቃቀም እንዲሁም በባህላዊ የአሠራሮች ምክንያት ከዘርፉ የሚገኘው ጥቅም የሚፈለገውን ያህል አጥጋቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህንን በማሻሻልና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ዘርፉን ለማሳደግ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያበጅም አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ጤና ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ዶ/ር አዱኛ ወዬሣ የምርምር ስራቸውን ሲያቀርቡ እንደገለፁት በሀገራችን በተለይ በስምጥ ሸለቆ ዝቅተኛ አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በወረርሽን መልክ ለሚከሰቱ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች በዝናባማ ወቅት የቅድመ መከላከል ሥራዎችን በመሥራት ተዛማች በሽታዎችን በእንጭጩ መከላከል  ይገባል ብለዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች፣ ዳይሬክተሮች፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ኢንስቲትዩቶች የመጡ ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡