በውሃ ህጎችና በውሃ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ

ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሥሩ ለሚገኙ የ2009 ዓ/ም የውሃ ምህንድስና ተመራቂዎችና የድህረ-ምረቃ ተማሪዎች እንዲሁም ከኢንስቲትዩቱ ለተጋበዙ ባለሙያዎች በውሃ ህጎችና የውሃ ፖለቲካ (hydro politics) ዙሪያ ግንቦት 12/2009 ዓ/ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጋበዙ ባለሙያ ሙያዊ ገለጻ አቅርቧል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ሣይንትፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በውሃው መስክ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ ባለሙያዎችን እያፈራ መሆኑን ጠቅሰው ተማሪዎቹ በዘርፉ የተሻለ ዝግጅት ኖሯቸው በየትኛውም መድረክ በእውቀት ላይ በመመርኮዝ ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በስልጠናው የሀይድሮ ፖለቲክስ ምንነትና ከአባይ ተፋሰስ ሀገሮች አንጻር ያለው ትንታኔ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር  ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ቀርቧል። ፕሮፌሰሩ በገለፃቸው ‘‘ድንበር ተሻጋሪ የውሃ አካላት በሞኖፖል የማይያዙና የሚያዋስኗቸው ሀገሮች በመተሳሰብና በመደራደር ለሁሉም የጋራ ጥቅም በሚሰጡበት መልኩ ሊጠቀሙባቸው የሚገባ የጋራ ሀብት ናቸው’’ ብለዋል።

በማህበረሰቡ  ዘንድ ይህ ግንዛቤ ዳብሮ ሀገሮች ትክክለኛ የውሃ አጠቃቀም ልምድ ቢኖራቸው በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና ልማት ተጠቃሚ ለመሆን ብሎም የተፋሰሱን ሀገራት ሠላምና ደህንነት ለማስከበር አይነተኛ ዘዴ መሆኑን ዶ/ር ያዕቆብ ገልጸዋል፡፡