"ልማትና ሠላም በደቡብ ኦሞ ዞን፦ የባህላዊ ግጭት አፈታት ሥነ-ስርዓት እንደ ማሳያ”

በደቡብ ኦሞ ዞን አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶች የልማት ሥራዎችና ሀገር አቀፍ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በአግባቡ እንዳይከናወኑ ተግዳሮት እየፈጠሩ ነው። ችግሩን አስመልክቶ ከዞኑ የተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት የተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶችን መሠረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲው የደቡብ ኦሞ የምርምር ማዕከል "ልማትና ሰላም በደቡብ ኦሞ ዞን፦ የባህላዊ ግጭት አፈታት ሥነ-ሥርዓት እንደ ማሳያ” በሚል ርዕስ ከግንቦት 25-26/2009 ዓ/ም የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል።

በችግሮቹ ዙሪያ የተለያዩ የጥናትና ምርምር እንዲሁም ማህበረሰብ ተኮር ሥራዎች ቢሠሩ ለሀገራዊ ልማት ያለው አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት በችግሮቹና በመፍትሄ ሀሳቦች ላይ ውይይት ለማድረግ መድረኩ መዘጋጀቱን የምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ እውነቱ ገልፀዋል፡፡

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ ባውዴ እንደገለጹት በዞኑ 16 ነባር እና ሌሎችም ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት ተከባብረው፣ ተረዳድተውና በጋብቻና በሌሎች ባህላዊ እሴቶች ተሳስረው እየኖሩ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ከአጎራባች ሀገራት፣ ክልሎች፣ ዞኖች እንዲሁም በዞኑ ብሄረሰቦች መካከል ግጭቶች ይከሰታሉ። ለአብነትም ከግጦሽ ሳር፣ ከውሃና ከዓሳ ማስገሪያ ቁሳቁሶች ዝርፊያ ጋር በተያያዘ በተነሱ ግጭቶች የንፁሀን ህይወት እየተቀጠፈ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ዞኑ ችግሩን ከምንጩ ለማጥፋት እየሠራ ቢሆንም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት አለማስገኘቱን የተናገሩት አስተዳዳሪው ዩኒቨርሲቲው ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ ምሁራን፣ መንግሥታዊ ተቋማትና የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነውን አርብቶ አደር በማሰባሰብና በጥናት የተደገፈ የመፍትሄ ሀሣብ በማቅረብ ላሳየው አጋርነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ መሰል ድጋፍና አጋርነቱ እንዳይለያቸውም ጠይቀዋል፡፡

የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበት አካባቢ የሀገሪቱ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ እንደመሆኑ ከፍተኛ ኃላፊነትና አደራ የተጣለበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይም የባህል ብዝሃነትን በምርምር፣ በማኅበረሰብ አገልግሎትና በሰው ኃይል የትምህርት ልማት ለማገዝ በሚደረገው ጥረት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ሠላም እና ልማት ያላቸው መስተጋብር፣ ባህላዊ ደንቦችና ሥርዓቶች ለሠላም ግንባታ ያላቸው ፋይዳ እንዲሁም የባህላዊ ግጭት አፈታት ሥነ-ሥርዓት ከሠላምና ልማት አንጻር በሀገራችንና በዞኑ ያለው ነባራዊ ሁኔታ በጥናታዊ ጽሑፍና በቡድን ውይይት በስፋት ተዳሰዋል፡፡ በተጨማሪም ከፌዴራል የአርብቶ አደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስቴር በመጡ ባለሙያዎች ‹‹የሠላም እሴት ግንባታ›› እና ‹‹የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ሥርዓት›› በሚሉ ርዕሶች ላይ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

የዩኒቨርሲቲውና ሌሎች ተጋባዥ ምሁራን፣ የኢፌዴሪ አርብቶ አደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስቴር ባለሙያዎች፣ የደቡብ ኦሞ ዞንና የወረዳዎች አመራሮችና የፍትህና ፀጥታ ኃላፊዎች እንዲሁም የጎሳ መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ውይይቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡