‹‹የከተሞች ዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር ለህዳሴያችን!››

7ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ‹‹የከተሞች ዘላቂ ልማትና መልካም አስተዳደር ለህዳሴያችን!›› በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚያዝያ 21-28 2009 ዓ/ም በጎንደር ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር በፎረሙ ላይ ተሳትፎ በማህበረሰብ አገልግሎት፣ በመረጃና ኮሚዩኒኬሽን እንዲሁም በሥነ-ህንፃና ከተማ ንድፍ ዘርፎች የተሠሩ ሥራዎችን ለህዝብ ዕይታ አቅርቧል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

መንግሥት ባስቀመጠው የከተማ ልማት ፖሊሲ በመመራት ከተሞች ዕድገታቸው በየጊዜው እየተሻሻለ መምጣቱን እንዲሁም በግብርና ላይ ለተመሠረተው ኢኮኖሚ የኢንደስትሪ ማቀነባበሪያ ማዕከላት በመሆን ለሚፈለገው የኢኮኖሚ ሽግግር ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል ገልጸዋል፡፡ የከተሞች ፎረም ከተሞች እርስ በእርሳቸው የሚማማሩበትና በውድድር ላይ  የተመሠረተ ዕድገት የሚያስቀጥሉበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ዘርፍ የውህድ የመታወቂያ ሥርዓት፣ የመኪና መቆጣጠሪያ ሥርዓት ንድፍና ትግበራ፣ የBSC/የውጤት ተኮር ሥርአት/ ትግበራ እና ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የሚሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶች በመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች አቶ ንዋይ ታደሰ እና በአቶ መስፍን ዳንኤል ለህዝብ ዕይታ አቅርቧል፡፡በሥነ-ህንፃና ከተማ ንድፍ ትምህርት ክፍል የተዘጋጁና በአርባ ምንጭ ከተማ ሊሠሩ የታቀዱ ህንፃዎችና ሌሎች ንድፎችም በትምርት ክፍሉ መምህራን በአቶ መሳፍንት ውሂብና አቶ አቤል ዓይናለም ለዕይታ ቀርበዋል፡፡

በተጨማሪም በማኅበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የተከናወኑ የተፋሰስና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎች፣ የማማከርና አጫጭር ስልጠናዎች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ላልተዳረሰባቸው ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣብያዎች የታዳሽ ኃይል አገልግሎት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የፈጠራ ባለመብትነት የተመዘገበው የጠብታ መስኖ የቴክኖሎጂ ሽግግርን አስመልክቶ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ ሸዋረታ ጌታቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ፎረሙ ከተሞች ምርጥ ተሞክሮዎችን የሚቀስሙበትና፣ መንግሥታዊ ተቋማት የከተማቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ስኬቶች የሚያሣዩበት፣ ልማታዊ ባለሀብቶች፣ የፈጠራ ባለሙያዎችና ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ መካከለኛ ባለ ሀብትነት የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች መልካም ተሞክሮዎቻቸውን የሚለዋወጡበትና ከሌሎች የልማት አጋሮቻቸው ጋር ትብብር የሚፈጥሩበት እንዲሁም ህዝቡን ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚያስችል መሆኑን ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡