17ኛው ዓለም አቀፍ ዘላቂ የውሃ ሀብት ልማት አውደ ጥናት ተካሄደ

ዩኒቨርሲቲው 17ኛውን ዓለም አቀፍ ዘላቂ የውሃ ሀብት ልማት አውደ ጥናት ከሰኔ 16-17/2009 ዓ/ም አካሂዷል፡፡

ውሃ ህይወት ከመሆኑ ባሻገር በኃይል ማመንጫ፣ በኢንደስትሪ፣ በመጓጓዣና በግብርና ዘርፎች እጅግ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን የገለፁት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ለውሃ ፍላጎት አለመጣጣምና ሌሎች ውስብስብ ችግሮች በዘርፉ የተሠማሩ ምሁራን ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡ የአውደ ጥናቱ መዘጋጀትም በምሁራን መካከል ሣይንሳዊ የልምድና እውቀት ልውውጥ እንዲኖር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡  ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የቴክኒክ አማካሪ ዶ/ር ሚካኤል መንክር በበኩላቸው መንግሥት የዜጎቹን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ብሎም የሀገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን በየዘርፉ ሰፋፊ ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅሟን ለማሳደግ ያላትን እምቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ልማት በማጎልበት ለጂቡቲና ሱዳን ስትሸጥ የቆየች ሲሆን የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ በቅርቡ ለኬኒያና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ዝግጅት እያደረገች ነው፡፡

የውሃና መስኖ ዝርጋታን በተመለከተ አበረታች ሥራዎች ቢኖሩም ከሚጠይቀው የገንዘብ መጠንና ከህብረተሰቡ ፍላጎት ጋር ተያይዞ ብዙ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አማካሪው ተናግረዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀትና ዘላቂ ምርምሮችን በማከናወን መንግሥት የጀመራቸውን የልማት ዕቅዶች አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በተደጋጋሚ በሥራ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ያወሱት የአውደ ጥናቱ ተሳታፊ በኬኒያ የኪባቢ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብት ኢንጂነር ዶ/ር ኢንግ ቤኔዲክት በአስተያየታቸው ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ለማጠናከር በዘርፉ የምታካሂዳቸው ቴክኖሎጂውን ያካተቱ ጥናቶችና  የምታሳየው ተነሳሽነት ሊበረታታ የሚገባ ነው ብለዋል፡፡

የመስኖ አውታሮች ዝርጋታ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ የከተማ የጎርፍ አደጋ መከላከያ ሞዴሎች፣ የለገዳዲ የውሃ ማቆሪያ የውሃ ጥራትና የፎቶፕላንክተን ለውጥ ሂደት፣ የአካባቢ አየር ንብረት ለውጥ በግብርና ምርትና በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ እና በሀዋሳ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች በአውደ ጥናቱ ከቀረቡ 25 ርዕሶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው የውሃ ሃብት ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ኢንጂነር አብደላ ከማል እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል በሚታወቅበት የውሃ ምርምር ዘርፍ በሀገር የልማት ሥራዎች አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ ምሁራንን እያፈራ የሚገኝ ሲሆን ምሁራኑ በሀገሪቱ ትላልቅ የውሃ ፕሮጀክቶች በመሳተፍ የበኩላቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር የተቀናጀ የውሃ አስተዳደር ፕሮጀክት በመቅረፅ በአባያና ጫሞ ሐይቆች ዘለቄታዊ ጥበቃ፣ ከደቡብ ዲዛይን ቁጥጥርና የግንባታ ክትትል ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር በደቡብ ኦሞ ዞን ወይጦ በረሃ አማራጭ የውሃ ምንጮች አቅርቦት እንዲሁም በአርባ ምንጭ ከተማ የኩልፎ ወንዝ የሚያደርሰውን የጎርፍ አደጋ በዘላቂነት ለመፍታት እየሠራ ነው፡፡ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ያቋቋመውን የውሃ ምርምር ማዕከል በምሁራን ለማደራጀት፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ተባብሮ ለመሥራትና በመሠል ሀገራዊ የምርምር ሥራዎች ላይ ተሳታፊ ለመሆን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

በአውደ ጥናቱ የኬንያ፣ ቤልጂየምና ፊንላንድ ምሁራንን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልልና የአርባ ምንጭና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን የምርምር ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡