የማጎ ፓርክ ህልውና የሁሉንም ትኩረት ይሻል!

የደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከል በዩኒቨርሲቲው መምህራንና ሌሎች አጥኚዎች በተዘጋጁ የጥናትና ምርምር ንድፈ ሀሣቦች ላይ የሚመክር መድረክ ሰኔ 19 ቀን 2009 ዓ.ም አሰናድቷል፡፡ የማጎ ብሔራዊ ፓርክ ህልውናና ቀጣይ ዕጣ ፈንታ በምክክር መድረኩ ሰፊ ሽፋን የተሰጠው ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በ1971 ዓ/ም የተቋቋው ማጎ ብሔራዊ ፓርክ 2,164 ስኩዌር ኪ.ሜ ስፋት የነበረው ሲሆን በቅርብ ጊዜ በአካባቢው በልማት ሥራ ምክንያት ይዘቱ ወደ 1,942 ስኩዬር ኪ.ሜ ዝቅ ብሏል፡፡ ከፓርኩ ምሥረታ ጀምሮ በጡረታ እስከተገለሉበት ጊዜ ድረስ በስካውትነት ያገለገሉት አቶ ገዛኸኝ አኩ ስለ ፓርኩ ሲናገሩ ‹‹በብዝሃ ህይወት ስብጥር በጥሩ ይዞታ ላይ የነበረ ሲሆን በ1983 የተካሄደውን የመንግሥት ሥርዓት ለውጥ ተከትሎ በተፈጠሩ ክፍተቶች በፓርኩ ዙሪያ ያለው ማህበረሰብ ወደ ፓርኩ ክልል ዘልቆ በመግባቱና ህገ-ወጥ አደን በመስፋፋቱ ህልውናው አደጋ ላይ ወድቋል›› ይላሉ፡፡ የመንግሥት ትኩረት ማነስ፣ የጥበቃ ሥርዓት መላላት እንዲሁም ከፓርኩ ከሚገኘው ገቢ የአካባቢው ህብረተሰብ በበቂ ሁኔታ ተጠቃሚ አለመሆን ችግሩን አባብሰውታል ብለዋል፡፡

ማጎ ብሔራዊ ፓርክ የደ/ብ/ብ/ህ/ክልላዊ መንግሥት ከሚተዳደሩ አምስት ብሔራዊ ፓርኮች አንዱና ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ መሆኑን የጠቀሱት የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ለማ መሠለ ህገ-ወጥ አደንና ለግጦሽ ሣር ወደ ፓርኩ ክልል በህገ-ወጥ መንገድ ዘልቆ መግባት የፓርኩ መሠረታዊ ችግሮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ህብረተሰቡ ፓርኩን በባለቤትነት መንፈስ ሊንከባከበው አለመቻሉና የግንዛቤ ችግሮች መኖራቸው የፓርኩ ህልውና አሳሳቢነት እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ክልሉ የተለያዩ መፍትሔዎችን ለመጠቀም የሞከረ ቢሆንም በጥበቃ ኃይሎች ብቻ ተፈላጊውን ለውጥ ለማምጣት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡

ህብረተሰቡ ከፓርኩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሥርዓት በመዘርጋት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወፍጮ ቤት፣ ትምህርት ቤት፣ ውሃ እና መሠል መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት መሞከሩን የገለፁት ም/ኃላፊው ፓርኩን ከማልማት አንፃርም ለመንገድ፣ ውኃና የፓርክ ጽ/ቤት፣ የእንግዳ ማረፊያ፣ የስካውቶች መኖሪያ ግንባታ የክልሉ መንግሥት በጀት መድቦ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ የፓርኩን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከላት ከመንግሥትና ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው ቢሠሩ ዉጤት ማምጣት የሚቻል መሆኑን አቶ ለማ ተናግረዋል፡፡

የማጎ ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ ጋናቡል ቡልሚ በበኩላቸው ፓርኩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የዱር እንስሳትን በህገ-ወጥ አደን ምክንያት እያጣ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በሙሉ አቅም ተንቀሳቅሶ የፓርኩን ህልውና ለማስቀጠልም ሆነ ሌሎች ሥራዎችን ለማከናወን በርካታ የመሠረተ ልማትና ሌሎች ችግሮች ጋሬጣ ሆነዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን ተወካዮች ለማወያየት የምክክር መድረኩን ማዘጋጀቱ የሚያስመሰግን መሆኑን ተናግረው መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች እስከ ታችኛው ማህበረሰብ ወርደው በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከልን ከተረከበ በኋላ ከመጋቢት 2007 ዓ/ም ጀምሮ በ6 የሥራ ክፍሎች በማዋቀር የመሠረተ ልማትና የፀጥታ፣ ቤተ-መጽሐፍት የማደራጀት፣ ያልተደራጁ የብሄረሰቦች ቅርሶችን የማሰባሰብ፣ ለተማሪዎችና ተመራማሪዎች ነፃ የኢንተርኔት አገልግሎት የመስጠት፣ የምርምር ርዕሰ ጉዳዮን ነቅሶ መውጣት እና ሌሎች ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ማዕከሉ የተለያዩ ምሁራንን በማሳተፍ በዞኑ መሠረታዊ ችግሮች ዙሪያ የምርምር ርዕሰ ጉዳዮችን የለየ ሲሆን ከርዕሰ ጉዳዮቹ መካከል የማጎ ብሔራዊ ፓርክ ወቅታዊ ችግሮችና ቀጣይ ዕጣ ፈንታ አንዱ መሆኑን የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ እሸቱ እውነቱ ተናግረዋል፡፡ ፓርኩን በተመለከተ በዞንና በወረዳ ደረጃ ለሚሠሩ ባለሙያዎች ማዕከሉ የገንዘብና የሙያ ድጋፍ እያረገ ሲሆን ይህ የምክክር መድረክ የፓርኩን ህልውና በዘላቂነት ለመታደግ መነሻ ሀሳቦችን ለማጠናከርና የሚመለከታቸውን አካላት ለማቀናጀት ይረዳል ብለዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የክልልና የዞን የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ ተመራማሪዎችና አመራሮች እንዲሁም የማጎ ፓርክ አዋሳኝ ማህበረሰቦች ተወካዮችና የጎሳ መሪዎች ተገኝተዋል፡፡