ዩኒቨርሲቲው ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ቀጣይነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለፀ

የዩኒቨርሲቲው የ2009 በጀት ዓመት የ12 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ ሐምሌ 7/2009 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በስትራቴጂክ ዕቅድ ክንውንና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዝሙ ቀልቦ በቀረበው ሪፖርት እንደተገለጸው በኢ-ለርኒንግ ተማሪዎችን ማስተማር፣ መፈተን እና ውጤት መግለጽ መጀመሩ፣ ከዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ አጋር ተቋማት ጋር በምርምር ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት መፈጠሩ፣ ከጤና ጥበቃ እና ከሣይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መ/ቤቶችና ከቤልጂዬም ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር መፈጠሩ፣ ዘርፈ ብዙ የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች መከናወናቸው፣ ከዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስር አኳያ ከኦሞ ኩራዝ ስኳር ኮርፖሬሽን ጋር ትስስር በመፍጠር የትምህርት ፕሮግራሞች ተቀርፀው የማስተማር ሥራ እየተከናወነ መሆኑ፣ ሠላማዊ የመማር ማስተማር አካባቢን መፍጠርና ውጤታማ የ1ለ5 የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሰራዊትን መገንባት መቻሉ በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ የላቁ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተጨማሪም ለሴቶች፣ ህፃናት፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች በጋሞ ጎፋ፣ በሰገን አካባቢ ሕዝቦች፣ በደቡብ ኦሞ ዞኖች እና በኮንሶ ልዩ ወረዳ በተቋቋሙ 5 ማዕከላት ነፃ የህግ ማማከርና ጥብቅና አገልግሎት መስጠት፣ በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚገኙ ት/ቤቶችን በትምህርት ቁሳቁሶችና በተከታታይ ስልጠና መደገፍ፣ ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች እንዲሁም ለአካባቢው ማህበረሰብ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎችን መስጠት፣ የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች፣ የጤና፣ የግብርናና የማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን በተሻለ አፈፃፀም ማከናወን በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

በሌላ በኩል በተቋራጮችና በአማካሪ ድርጅቶች ምክንያት የግንባታ ሥራዎች መዘግየት፣ የፋይናንስና የግዥ ሥርዓት የተቀላጠፈ አለመሆን፣ የመብራትና የውሃ አቅርቦት ችግሮች፣ የማስተማሪያ ሆስፒታል ግንባታ ባለመጠናቀቁ በህክምናና ጤና ሣይንስ ትምህርት አሰጣጥ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩና በዚህም ለአላስፈላጊ ወጪ መዳረግ እና የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና የባህል ብዝሃነት ዘርፎች በተፈለገው ደረጃ አለመጠናከር የታዩ ክፍተቶች እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደተናገሩት የማስፋፊያ ግንባታዎች፣ ዓለም አቀፋዊነት፣ የድህረ-ምረቃ ተማሪዎችን ቁጥር ማሳደግ፣ የሴቶች ተሳትፎ ማጎልበቻ ሥራዎች፣ የቅድመ ምረቃና ድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞችን ማስፋፋት፣ የመምህራን ልማትና የመማር ማስተማር ሂደትን ሠላማዊና ውጤታማ ማድረግ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከሚሠሩ ተግባራት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ያስመዘገባቸውን ስኬቶች ቀጣይነት ማረጋገጥ እንዲሁም በአንዳንድ አፈፃፀሞች ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶች ተለይተውና በቀጣዩ በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ተመለክተው መፈፀም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም የ2010 በጀት ዓመት ዕቅድ ለዩኒቨርሲቲው ሴኔት ቀርቦ በጥልቀት ተተችቷል፡፡