አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2010 ዓዲስ ዓመት አቀባበልን በልዩ ሁኔታ አከበረ

መጪውን አዲስ ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ በልዩ ሁኔታ ለመቀበል በታቀደው መሠረት ዩኒቨርሲቲው በዓሉን በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ከነሀሴ 30 ቀን ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት አክብሯል፡፡  ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የዩኒቨርሰሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በዓሉን አስመልክተው ሲናገሩ ባለፉት አሥርት ዓመታት በሀገር ዓቀፍ ደረጃም ሆነ በዩኒቨርሲቲው በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አውስተው ነገር ግን ባሳለፍነው ዓመት ያስተናገድናቸው አንዳንድ አለመረጋጋቶች ስኬቶቹን የሚያደበዝዙና የሀገሪቱ ገጽታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደሩ ነበሩ ብለዋል፡፡

ይህንን ተፅዕኖ በማስወገድ ወደ ቀደመ የሠላምና የመቻቻል ዓውድ በመመለስ ልዩነቶችን የሚያስተናግድ፣ ሀገራዊ ፍቅር ያለውና አንድነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ በመፍጠር የራሱን ድርሻ ለመወጣት ዩኒቨርሲቲው የአዲስ ዓመት ልዩ የአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱን ማዘጋጀቱን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡ አዲሱ ዓመት የሠላም፣ የፍቅርና የእድገት እንዲሆንም በዩኒቨርሲቲው ስም የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በልዩ የአዲስ ዓመት አቀባበል ፕሮግራሙ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ህብረተሰብ በማሳተፍ የደም ልገሳ፣ የችግኝ ተከላ የአካባቢ ጽዳት እና ለአቅመ ደካማ አዛውንቶችና ህፃናት የአልባሳት ማሰባሰብና ልገሳ ፕሮግራሞችን ያከናወነ ሲሆን ለዩኒቨርሲቲውና ለአካባቢው ማህበረሰብ የመልካም ምኞት መግለጫ ካርዶችን አበርክቷል፡፡

የፕሮግራሙ ታዳሚዎች በአስተያቶቻቸው ዩኒቨርሲቲው የፍቅርና የአንድነት መድረኩን አዘጋጅቶ አዲሱን ዓመት በልዩ መንፈስ እንድንቀበል ማድረጉ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል፡፡ በተለይም የአንድ ሰው ህይወት ሊያተርፍ የሚችል ደም በመለገስ ዓዲሱን ዓመት መቀበላቸው እጅግ ያስደሰታቸው መሆኑን ተናግረው ወደፊትም ይህን በጎ ተግባር ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት