ዩኒቨርሲቲው ከ Netherlands Initiative for Capacity Development in Higher Education (NICHE) ጋር በመተባበር በዋነኛነት ከውኃ ሀብትና መስኖ ምህንድስና ትምህርት ክፍልና ሌሎች ሁለት ትምህርት ክፍሎች ለተወጣጡ መምህራንና የሥራ ኃላፊዎች ከነሀሴ 23-25/2009 ዓ.ም በራዕይ ልማት ላይ ያተኮረ ሥልጠና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሰጥቷል፡፡

በማያቋርጥ የመማርና የመለወጥ ሂደት ውስጥ ያለ ተቋም (Learning Organization) ምንነት፣ ገፅታዎችና መሠረታዊ ፅንሰ ሀሣቦች በአሰልጣኝ ዶ/ር ሄንክ ቫን ደን ትንታኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

አሰልጣኙ የታዋቂውን ፀሐፊ ፒተር ሰንጌ ‘The Fifth Discipline’ የተሰኘ መጽሐፍ ጠቅሶ እንዳስረዳው በማያቋርጥ የመማርና የመለወጥ ሂደት ውስጥ ያለ ተቋም (Learning Organization) ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች አቅምና ችሎታቸውን እያሳደጉ በግል ያካበቱትን ዕውቀትና ግኝት ለሙያ አጋሮቻቸው በማካፈል የተቋሙን ራዕይ በጋራ ለማሳካት ይጥራሉ፡፡

የተቋም የማያቋርጥ ትምህርትና ለውጥ በአምስት መሠረታዊ ምሰሶዎች ላይ የተመረኮዘ ሲሆን እነዚህም ተቋሙን በትንንሽ መዋቅሮች እንደተገነባ አንድ ውስብስብ ሥርዓት ወስዶ መዋቅሮቹንና ሥርዓቱን ለመረዳት መሞከር (System Thinking)፣ ግለሰባዊ ጥረትና ስኬት (Personal Mastery)፣ ዓለምን ለመረዳትና እርምጃ ለመውሰድ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ በጥልቅ የተዋቀሩ አእምራዊ ምስሎች፣ ግምቶችና ማጠቃለያዎች (Mental Models)፣ የጋራ ራዕይ (Shared Vision) እና የጋራ ራዕይን ለማሳካት በጋራ ማሰብና መማማር (Team Learning)ናቸው፡፡

እነዚህን መሠረታዊ ነጥቦች ይዘው ሠልጣኞች ፅንሰ ሀሳቦቹን ይበልጥ ለመረዳት በሚያስችል መልኩ የቡድን ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ እያንዳንዱ ቡድን በተሰጠው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያጠናቀረውን ሀሣብ ለተቀሩት በማካፈል ሀሳቡ በጥያቄና አስተያየት እንዲዳብር የጋራ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ለውኃ ሀብትና መስኖ ምህንድስና ትምህርት ክፍልና ለዩኒቨርሲቲ የውኃ ሴክተር ትብብር የጋራ ራዕይ በማርቀቅ ሥልጠናው ተጠናቋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ የሥልጠናውን ፋይዳ ሲናገሩ ‹‹ኢንስቲትዩቱ ብሎም የውኃ ሀብትና መስኖ ምህንድስና ትምህርት ክፍል ወደሚፈለው ደረጃ እንዲደርስ ትክክለኛ ራዕይ ሊኖረው ግድ ነው፡፡ ይህ ሥልጠናም ራዕያችንን ለመቅረጽ ጉልህ ድርሻ አበርክቷል›› ብለዋል፡፡

አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በተገቢው መልኩ የሚያስተዳድር በቂ እውቀት ያለው የሰው ኃይል እጥረት ያለ በመሆኑ ብዙ ጊዜ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ውጤታማ ሳይሆኑ እንደሚቀሩ የተናገሩት ዳይሬክተሩ ይሄንን ክፍተት ለመሙላት ትክክለኛ ሥርዓተ ትምህርት ቀርፆ በበቂ የማስተማሪያ ግብዓቶች ብቁ ተማሪዎችን ለማሰልጠን ትምህርት ክፍሉ የጠራና ጠንካራ ራዕይ ሊኖረው የሚገባ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

The Netherlands Initiative for Capacity development in Higher Education (NICHE) በኔዘርላንድስ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት የልማት ትብብር ፕሮግራም ሲሆን በውኃና የምግብ ዋስትና፣ የሥነ ተዋልዶ ጤናና መብቶች፣ በደህንነትና የህግ የበላይነት እንዲሁም በታዳጊ ሀገራት የከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማትን ብቃት ለማሳደግ ይሠራል፡፡ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ በትምህርት፣ በግብርና እና በአካባቢ (የተፈጥሮ ሀብት አያያዝና ኢኮ ቱሪዝም) ዘርፎች ትኩረት አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡