አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለነባር ተማሪዎች በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የሚተገበረውን ግምገማዊ ሥልጠና ከመስከረም 25-27/2010 ዓ.ም አካሄደ

በጥልቅ ተሃድሶ ውይይት ወቅት የተለዩ ችግሮችና ተግዳሮቶችን መነሻ በማድረግ የትምህርት ዘመኑ ከመጀመሩ በፊት ለሀገራዊ ህዳሴና ለልማት ስኬቶች መፋጠን የጋራ መግባባት ለመፍጠር እና በሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት ብቁና ሀገር ወዳድ ምሩቃንን ከማብቃት አንፃር ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሥልጠናው በሀገር አቀፍ ደረጃ መዘጋጀቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልፀዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

ሥልጠናው እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት ከተሰጠው የትምህርት ጥራትና አግባብነት ጋር ተያይዞ በተማሪው አመለካከት፣ ክህሎትና የትምህርት ተነሳሽነት እንዲሁም በመማር ማስተማር ዙሪያ ያሉትን ክፍተቶች በመለየትና በመፈተሽ የሚጠበቅባቸውን ስኬትና የሚኖራቸውን ድርሻ እንዲወስዱ የሚያደርግ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የውጤታማ ትግበራ ስኬት አሠራር ሥርዓት ግንባታ፣ ሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር፣ በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት የተነሱ ችግሮች፣ የተፈቱና ቀሪ ሥራዎች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የ2009 ትምህርት ዘመን አፈፃፀምና የ2010 የትምህርት ዘመን ዕቅድ ሰነዶች በሥልጠናው ወቅት ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የ4ኛ ዓመት የውሃ ሀብትና መስኖ ምህንድስና ትምህርት ክፍል ተማሪ ፀደይ ሙሉጌታ ሥልጠናውን አስመልክቶ በሰጠችው አስተያየት እንደ ተማሪም ሆነ እንደ ዜጋ የሚጠበቅብንን አውቀን በመማር ማስተማር ሂደትና በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን በሚኖረን እንቅስቃሴ ተግባራዊ እንድናደርግ የሚረዳን ነው ብላለች፡፡ ተማሪዎች የመልካም ሥነ-ምግባር አርአያ በመሆን ከመምህራን፣ ከሌሎች ተማሪዎችና ከዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ጋር በመግባባት ለመዝለቅ የሚያስችላቸውን ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መሆኑንም ተናግራለች፡፡

የትምህርት ክፍሉ የ3ኛ ዓመት ተማሪ ካሣሁን ደርበው በበኩሉ ተማሪዎች የነገ ሀገር ተረካቢዎች እንደመሆናችን መጠን በእውቀትና በክህሎት ራሳችንን ዝግጁ አድርገን መውጣት አለብን ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የውጤታማነት ትግበራ አሠራርን ከወዲሁ ማወቃቸው ቅድሚያ መሰጠት ላለበት ሥራ ቅድሚያ ሰጥተው ለውጤታማነትና ለለውጥ እንዲዘጋጁ የሚያደርጋቸው መሆኑን ገልጿል፡፡

ሥልጠናውን 14 ሺህ 33 የዩኒቨርሲቲው ነባር ተማሪዎች በሁሉም ካምፓሶች ተከታትለዋል፡፡