ዩኒቨርሲቲው ከአምሬፍ ሄልዝ አፍሪካ ጋር በመተባበር በሁሉም ካምፓስ በሚገኙ ክሊኒኮች ለሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች እና ለሁሉ ዓቀፍ ሴክተር የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ኦፊሰሮች በሥነ-ተዋልዶ ጤና እና በኤች አይ ቪ/ኤድስ ወጣት-ተስማሚ የጤና አገልግሎት ከጥቅምት 15-16/2010 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የሁሉ ዓቀፍ ሴክተር የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ መርክነህ መኩሪያ እንደገለፁት የሥልጠናው ዓላማ የሥነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮችንና ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ያሉ ውስንነቶችና ክፍተቶች ላይ በመወያየት የጤና ባለሙያዎቹ ግንዛቤያቸው እንዲያድግና በየካምፓሱ ወጣት-ተስማሚ የሥነ-ተዋልዶ ጤና አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ነው፡፡ ሥልጠናው የሥነ-ተዋልዶ ጤና ክሊኒክ፣ የሪሶርስ ሴንተርና የዜሮ ፕላን አስፈላጊነት እና ትግበራ ላይ የጠራ ግንዛቤን ይፈጥራል፡፡

የሥነ-ተወልዶ ጤና ክሊኒክ በቋሚነት መኖሩ፣ በተሟላ ግብዓትና ባለሙያ መደራጀቱ፣ ወጣት ተኮርነቱ፣ የባለሙያዎች አካላዊና አዕምሯዊ ዝግጁነት፣ የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም ምስጢር ጠባቂነትና ነፃነት ላይ ሠልጣኞች ውይይት አድርገዋል፡፡

የአምሬፍ ሄልዝ አፍሪካ አስተባባሪ አቶ በጥበቡ ሙሉጌታ እንደተናገሩት ምሥረታና መቀመጫው ኬንያ የሆነው አምሬፍ ሄልዝ አፍሪካ በኢትዮጵያ 30 ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በዋነኛነት የሥነ- ተዋልዶ ጤናን ለማሻሻል ይሠራል፡፡ ፕሮጀክቱ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ውል ገብቶ የአቅም ማጎልበት፣ የጥናትና ምርምር፣ የግብዓት የማሟላት እና ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ የጤና አገልግሎቶች የመስጠት ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡