ወጥ የሆነ የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት የተዘጋጀ የአሠራር ማዕቀፍ ላይ ውይይት ተካሄደ

የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ከኮሌጅ ዲኖችና ከየትምህርት ክፍሉ ኃላፊ መምህራን ጋር ለዩኒቨርሲቲው ሴት ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት አሰጣጥን አስመልክቶ ጥቅምት 21/2010 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ውስጥ የሚታየውን የሥርዓተ-ፆታ ክፍተት ለማጥበብ የተለያዩ አሠራሮች የተዘረጉ ሲሆን የማጠናከሪያ ትምህርት አንዱ ነው፡፡ በማጠናከሪያ ትምህርት አሰጣጡ ውጤት እየተመዘገበ ቢሆንም በአፈፃፀሙ ላይ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎና ውጤታማነት በማጎልበት ሴት ተማሪዎች በሀገራቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ እድገት የሚኖራቸውን ሚና በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ የማሳደግ ድርሻውን በመወጣት ላይ ነው፡፡ ስለሆነም በዩኒቨርሲቲው በተለያየ መልኩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማና ብቁ እንዲሆኑ ወጥ የሆነ የአሠራር ማዕቀፍ በመዘርጋት እየተሰጠ ያለውን የማጠናከሪያ ትምህርት የበለጠ ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

‹‹ወጥ የሆነ የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት የተዘጋጀ የአሠራር ማዕቀፍ››፣ ‹‹የሴቶች ትምህርት ፎረም ማቋቋሚያና አተገባበር መመሪያ›› እና ‹‹የወንዶች አጋርነት ለፆታ እኩልነት›› የሚሉ ርዕሶች ላይ የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሰለ መርጊያ ገለፃ ያቀረቡ ሲሆን ማብራሪያውን መሠረት ያደረጉ ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ተነስተው በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ ከተማሪዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በድጋፍ አሰጣጥ ዙሪያ የውይይት መድረኮችን ማመቻቸት፣ ተማሪዎች ድጋፉን በትክክል እየተጠቀሙ ስለመሆናቸው ከትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ ከመምህራን፣ ከሴት ተማሪዎች ክበብና ከተማሪዎች ህብረት ተጠሪ ጋር በየወቅቱ መከታተል፣  በሚመርጧቸው ኮርሶች ዙሪያ እገዛ ማድረግ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት የሚሰጡ ተማሪዎችን ማስተባበር፣ በድጋፍ አሰጣጥ ወቅት ያጋጠማቸውን ችግሮች በመለየት ማሳወቅ እና በጀት ማፈላለጊያ ፕሮጀክቶችን መቅረፅ በተቋማዊ ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት በኩል የሚተገበሩ ሥራዎች መሆናቸው ለአብነት ተጠቅሷል፡፡