የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ት/ምህርት ክፍል አዲስ ገቢ ተማሪዎች አቀባበልና ‹‹የኢትዮጵያ ሜካኒካል ኢንጂነሮች፣ ተማሪዎችና መምህራን ማኅበር በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ›› ምሥረታን አስመልክቶ ጥቅምት 30/2010 ዓ/ም የእንኳን ደስ አላችሁ ፕሮግራም አዘጋጅቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ መ/ር ሀብተወልድ አባቡ እንደገለፁት የማኅበሩ መመሥረት የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎችና መምህራን በቴክኖሎጂ የታገዘ እውቀት እንዲኖራቸው፣ በትምህርት ክፍሉ የሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎች ለሌሎች ሞዴል እንዲሆኑ እና ተመራቂ ተማሪዎች ከሥራ ጠባቂነት አስተሳሰብ ወጥተው ሥራ በመፍጠር ከራሳቸው አልፈው ሀገራቸውን የሚጠቅሙበትን ምቹ  ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

ማኅበሩ በ2010 ዓ/ም የሀገር ዓቀፉ የኢትዮጵያ ኢንጂነሮች ማኅበር አባልነት ፈቃድ ያገኘ መሆኑን የገለፀው የማኅበሩ መሥራች የ5ኛ ዓመት የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የአብፀጋ አበረ የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎችና መምህራን በኢትዮጵያ ካሉ ኢንደስትሪዎች ጋር የቴክኖሎጂ ትውውቅ እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው ብሏል፡፡ የ3ኛ ዓመት የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ አበበች መኩሪያ በበኩሏ የማኅበሩ መመሥረት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ጋር የልምድና የእውቀት ልውውጥ እንዲኖር ከማስቻሉም በተጨማሪ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ የመፍጠር ክህሎታቸው እንዲዳብር የሚያግዝ መሆኑን ተናግራለች፡፡

የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ የሙያ ሥነ-ምግባርን ማክበር፣ ሙያውን ከቴክኖሎጂ ጋር ማስተዋወቅ፣ ለባለሙያዎች የሚገባቸውን ክብር መስጠት፣ ለሀገሪቱ የኢንደስትሪ እድገትና የማምረቻ መሣሪያዎችን ለመጠቀም በሚደረጉ ጥረቶች ትኩረት ሰጥቶ መሥራት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሮችን ማበረታታት እንዲሁም የተማሪዎችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ማጠናከር የማኅበሩ መመሥረት ዓላማዎች ከሆኑት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በሜካኒካል ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል 1,235 የሚሆኑ ከ1ኛ -5ኛ ዓመት ተማሪዎች ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ እንዲሁም ፕሮዳክሽን ኢንጂነሪንግ የትምህርት ፕሮግራሞችን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡