የከፍተኛ ዲፕሎማ መርሃ - ግብር ስልጠና ተጀመረ

የሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህርይ ሣይንስ ት/ቤት ለ245 የዩኒቨርሲቲው መምህራን የከፍተኛ ዲፕሎማ መርሃ - ግብር "Higher Diploma Program"(HDP) ስልጠና ከጥቅምት 27/2010 ጀምሮ በዋናው ግቢ፣ ጫሞ፣ አባያና ነጭ ሣር ካምፓሶች መስጠት ጀምሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የትምህርት ቤቱ ዲን ዶ/ር ኢዮብ አየነው እንደገለፁት መምራን በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የተለያዩ ዕውቀቶችን ይዘው ቢወጡም መምህርነት፣ የማስተማሪያ ዘዴ እና የክፍል አያያዝ ላይ ግንዛቤ የሌላቸው በመሆኑ ስልጠናው መሠረታዊ የማስተማር ዕውቀት፣ አቅምና ሥነ - ዘዴ በማዳበር በማስተማር ክህሎት ብቁ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡

ስልጠናው በ4 ሞጁሎች ላይ ያተኮረና ለ192 ሰዓታት የሚሰጥ ሲሆን የመማር ማስተማር ሂደት፣ የክፍል አያያዝ፣ የት/ቤት አደረጃጀትና ምደባ፣ ሴት ተማሪዎችን ማብቃት እንዲሁም በመማር ማስተማር ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ምርምሮችን ማካሄድ በስልጠናው ይዳሰሳሉ፡፡

መምህራን የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመው የማስተማር ብቃታቸውን በማሻሻል የተማሪዎችን የመቀበል ክህሎት ለማዳበርና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት መሥራት የሚጠበቅባቸው መሆኑን የከፍተኛ ዲፕሎማ ፕሮግራም አስተባባሪ  መ/ር አንለይ ብርሃኑ  አሳስበዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዋቻሞና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በአርባ ምንጭና ሆሳዕና መምህራን ትምህርት ኮሌጆች በከፍተኛ ዲፕሎማ መርሃ - ግብር አስተባባሪነት እየሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡