የደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ከአ/ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትሥሥርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ጋር በመቀናጀት የዩኒቨርሲቲውን ጂኦሎጂ(የሥነ-ምድር ሣይንስ) ት/ክፍል ባለሙያዎች አዋቅሮ በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ያከናወነውን የማዕድን ዳሰሳ ጥናት ግኝት ኅዳር 04/2010 ዓ/ም በሀዋሳ ከተማ አቅርቧል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የውይይት መድረኩን የመሩት የደ/ብ/ብ/ህ/ክ መንግሥት የውሃና መስኖ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ እንደገለጹት ኤጀንሲው ከአርባ ምንጭ እና ዲላ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት በሲዳማ ዞን በንሳ እና አሮሬሳ እንዲሁም በሰገን አካባቢ ህ/ዞን በቡርጂና ኮንሶ አካባቢዎች መነሻ ጥናቶች እያካሄደ ነው፡፡ በአካባቢዎቹ ለኢንደስትሪ ግብዓትና ለጌጣጌጥ የሚያገለግሉ እንዲሁም እንደ ወርቅ ያሉ ውድ ማዕድናት መኖራቸውን መነሻ ጥናቶቹ ያመለክታሉ፡፡ በግንባታና በኢንደስትሪ ማዕድናት ላይ በአነስተኛና ጥቃቅን የሚደራጁ ወጣቶችን በማሳተፍ ተጠቃሚ ለማድረግ የልየታ ሥራ የተሠራ ሲሆን ውድ በሆኑና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በሚጠይቁ ማዕድናት መገኛ ጠቋሚ ቦታዎች ላይ የግል ባለሀብቱ ተሠማርቶ ተጨማሪ የአሰሳ ጥናት በመሥራት ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚደረግ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት በ2010 በጀት ዓመት 40,000 ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማሰማራት ታቅዶ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 3,000 ወጣቶች ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ወጣቶቹ የማምረት ሂደት እንዲጀምሩ የማደራጀት እና የክህሎት ሥልጠና ሥራዎች የሚሠሩ ሲሆን ለዚህም የፌዴራል ማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ባለሙያዎች የክህሎትና የዕውቀት ክፍተት ባለበት ቦታ ድጋፋቸውን ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

በጥናት ውጤቱ እንደተመለከተው በተለይ የጌጣጌጥና ውድ ማዕድናት በባህላዊ መንገድ እየተመረቱ የግብይት ሥርዓት ሳይከተሉና ለማዕከላዊ ገበያ ሳይቀርቡ ወደ ጎረቤት ሀገራት ይሻገራሉ፡፡ ይህንን ህገ ወጥ አሠራር ለማስወገድ የበርካታ ባለሀብቶችን የግንባታ ማዕድናት ፈቃድ በመሰረዝ በህጋዊ መንገድ ለተደራጁ ወጣቶች የማስተላለፍ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ በተጨማሪም በህገ ወጥ መንገድ የሚወጡ ውድ ማዕድናትን ለመከላከል ከንግድና ኢንደስትሪ ቢሮ፣ ገቢዎች ባለሥልጣንና ፖሊስ ጋር የጋራ ፎረም በመመሥረት በተቀናጀ መልኩ ለመከላከል ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ኢንደስትሪ ትሥሥርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ደሳለኝ ጃራ ዳይሬክቶሬቱ ከተቋቋመ አጭር ጊዜያትን ያስቆጠረ ቢሆንም ከተለያዩ ተቋማት ጋር ትብብር ፈጥሮ በርካታ ጅምር ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የዛሬው የጥናት ግኝትም ከትሥሥር ውጤቶቹ አንዱና እንደ ትልቅ ስኬት የሚቆጠር ነው ብለዋል፡፡