ለተግባር ትምህርት ትኩረት መሰጠቱ የፈጠራና የምርምር ክህሎታቸው እንዲጨምር እንደሚያግዛቸው ተማሪዎች ገለፁ

የ6ኛ ዓመት የሥነ-ህንፃና ከተማ ፕላን ተማሪዎች ለተግባር ትምህርት የሚያግዟቸውን የሥነ-ህንፃና ቅርስ ጥበቃ ኮርሶችን አስመልክተው በኮንሶ ባህላዊና መልክዓ ምድራዊ ቅርሶች ኅዳር 01/2010 ዓ.ም ትምህርታዊ ጉብኝት አካሂደዋል፡፡ ተማሪዎቹ ከትምህርታቸው ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የኮንሶ ባህላዊ ጎጆ ቤቶችና ባህላዊ የእርከን ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው የመረጃ ማሰባሰብ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የሥነ-ህንፃና ከተማ ፕላን ት/ክፍል መ/ር ሀጎስ አማን እንደተናገሩት የጉብኝቱ ዓላማ ተማሪዎች በንድፈ-ሀሣብ የተማሯቸውን የሥነ-ህንፃና ቅርስ ጥበቃ ኮርሶች በተግባር እንዲያጠናከሩ፣ በቅርሶች ጥበቃና ጥገና ላይ የሚታዩ ችግሮችን በምርምር በመለየት የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያስቀምጡ እንዲሁም የአካባቢው ህብረተሰብ ባህሉን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያስተላልፍ የማንቂያ ደወል ማሰማት ነው፡፡ ባህልን እያጠፉ ዘመናዊነት የሚታሰብ አይደለም ያሉት መ/ር ሀጎስ በአንዳንድ ባህላዊ መንደሮች ባህላዊ ጎጆዎችን በዘመናዊ የመቀየሩ ሥራ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ቅርሶቹ ዘመናዊነት ሳይበርዛቸው ተጠብቀው እንዲቆዩ ዩኒቨርሲቲው ሣይንሳዊ ምርምሮችን በማካሄድ የተሻለ የሚሠራ ይሆናል፡፡

የኮንሶ ባህላዊ ቅርሶች ጥንታዊ ይዘት ያላቸው መሆኑ፣ የቅርሶቹ ምሉዕነት፣ ቅርሶቹ ባህላዊ የህግና የአስተዳደር ሥርዓት የተዘረጋላቸው መሆኑ በUNESCO እንዲመዘገቡ ምክንያቶች መሆናቸውን የገለፁት የኮንሶ ባህላዊ ቅርሶች ጥናትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ሻካይቶ ሮባ የቅርሶቹን ደህንነት ጠብቆ ለማቆየት ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ያሳተፉ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን የበኩሉን ሚና መጫወት ይገባዋል ብለዋል፡፡

የ6ኛ ዓመት የሥነ-ህንፃና ከተማ ፕላን ተማሪ ቢላር ዋበና እና ዛይድ ገ/ክርስቶስ እንደተናገሩት የመስክ ጉብኝቱ በንድፈ-ሀሣብ የተማሩትን ከተግባር ጋር በማዋሃድ የእውቀታቸውን ደረጃ እንዲገመግሙ ከማስቻሉም ባሻገር እውቀትና ክህሎታቸውን ተጠቅመው ለነገው ትውልድ ተስፋ የሆኑ ቅርሶች ደህንነት በመጠበቅ ረገድ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ይረዳቸዋል፡፡

የኮንሶ ባህላዊና መልክዓ ምድራዊ ቅርሶች በUNESCO እንዲመዘገቡ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከቱት የኮንሶ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ባለሙያ አቶ ኩስያ ሻንቀሬ ጉብኝቱ ተማሪዎቹ በክፍል ውስጥ የተማሯቸውን ቅርሶች በአካል አይተው እንዲደነቁ ከማስቻሉም በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበረሰብ ቅርሶቹ በሀገርም ሆነ በዓለም ደረጃ ቢጎበኙ የሚወደዱና ተፈላጊ ሀብቶች ናቸው የሚል መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡