የቼክ ሪፐብሊኩ ሜንደል ዩኒቨርሲቲ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመጣመር በሁሉን አቀፍ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ላይ የሁለት ቀናት ጉባኤ አካሂዷል፡፡

የእንስሳት እርባታ የግጦሽ መሬትን በማይጎዳ መልኩ ማካሄድ፣ የአፈርና ውኃ ዕቀባ፣ የመሬት ለምነትን በማሻሻል ምርታማነትን ማሳደግ፣ የመሬት መሸርሸርን መከላከልና መሰል የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ላይ ያተኮሩ ጥናቶችና ተግባራዊ ተደርገው ውጤት ያስገኙ ተሞክሮዎች ቀርበው ውይይትና የልምድ ልውውጥ ተደርጓል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ የተራቆተ መሬት የተቀናጀ መልሶ ማልማት ሥራ ተግባራዊ ከተደረጉ ጥናቶች አንዱ ነው፡፡ ተሞክሮውን ያቀረቡት የሜንደል ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ዶ/ር ሽፈራው ዓለም እንደተናገሩት በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ በከፍተኛ የህዝብ ቁጥር እና በእርሻ መሬትና የግጦሽ መስፋፋት ምክንያት የተራቆተ መሬት መልሶ እዲያገግም ተደርጓል፡፡ በአካባቢው 7 ሺህ ሜትር ኪዩብ መለስተኛ የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓዶች እና 60 ሺህ ትንንሽ እርከኖች ተገንብተው የዝናብ ውሃን እንዲይዙ የተደረገ ሲሆን ለቦታው ተስማሚ የሆኑ የዛፍ ዝርያዎችም ተተክለዋል፡፡ በቼክ ሪፐብሊክ የገንዘብ ድጋፍ 11 ሚሊየን ብር የተመደበለት ፕሮጀክት በ3 ዓመት አፈፃፀሙ 140 ሄክታር የተጎዳ መሬት የተሸፈነ ሲሆን ይህም 21 ሺህ ህዝብ ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ አካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አጌና አንጁሎ በተለያዩ ምክንያቶች የሀገሪቱ የደን ሽፋን መመናመን እና የመሬት መራቆት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ገልፀው በዚሁ ከቀጠለ ሐይቆቻችን በደለል እየተሞሉ በቀላሉ ወደ መጥፋት ደረጃ ይደርሳሉ ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ከጥናትና ምርምሮች ባሻገር አፋጣኝ ተግባራዊ እርምጃ የሚጠይቅ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ኢንስቲትዩቱ በተራቆቱ መሬቶች ላይ ያሉ የተለያዩ የእጽዋት ዝርያዎች መልሰው እንዲያገግሙ አልያም በአዳዲስ የዛፍ ዝርያዎች የመተካት ሥራ እየሠራ ነው፡፡

ህብረተሰቡ ለእንጨት ፍላጎቱ የተፈጥሮ ደንን እንዳይጠቀም አማራጭ የማገዶ ደን ተከላ እና ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችና አማራጭ የኃይል ምንጮችን ማስተዋወቅ የሚያስፈልግ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር አጌና በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ፈጣን የመፍትሔ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲዎች ዋነኛ የማገዶ እንጨት ተጠቃሚ በመሆናቸው ከተለመደ አሠራር የመውጣት ቁርጠኝነት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ስምኦን ሽብሩ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከሜንደል ዩኒቨርሲቲ ጋር በጥምረት ለመሥራት የ5 ዓመት የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን ገልፀው በዋናነት የተፈጥሮ ሀብትን ከመንከባከብ፣ ከአፈርና ውኃ ጥበቃ፣ የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ከማድረግና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንፃር በተለይ አነስተኛ የእርሻ ማሳ ያላቸው የሀገራችን አርሶ አደሮች አፈርና ውኃን በማቀብ ምርታማነታቸውን ማሻሻል እንዲችሉ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡

በጉባኤው በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ ም/አምባሳደርን ጨምሮ የሜንደል እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡ በጉባኤው ማጠናቀቂያም በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የጫኖ ሚሌ የችግኝ ማባዣና የሥልጠና ማዕከል እና በአቅራቢያው በሚገኝ ተራራ ላይ የተሠራ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራን ጎብኝተዋል፡፡