ሣውላ ካምፓስ 8 የምርምር ንድፈ ሀሣቦችን አቀረበ

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሣውላ ካምፓስ የአካባቢው ኅብረተሰብ መሠረታዊ ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረጉ 8 የምርምር ንድፈ ሀሣቦች ኅዳር 15/2010 ቀርበው ተተችትዋል፡፡

የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ የሰሊጥ ምርትና ምርታማነት፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተግባቦት ክህሎት እንዲሁም ከሞሪንጋ ተክል ነዳጅ መሥራት ከቀረቡ የምርምር ንድፈ ሀሣቦች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ምርምሮቹ ተግባራዊ ሲደረጉ ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተገልጿል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የአካባቢው ማኅበረሰብ በግብርና ሥራ የሚተዳደርና በተለይም ሰፊ የሰሊጥ ምርትና አቅም ያለው ቢሆንም የገበያ ትስስርሩ ደካማ በመሆኑ አምራቹ በዛ ልክ ተጠቃሚ አለመሆኑን የሣውላ ካምፓስ ዲን አቶ ገ/መድህን ጫሜኖ ገልፀዋል፡፡ የጥናት ንድፈ ሀሣቦቹ ይህንን በተግባር በማሳየት መፍትሄዎችን የሚጠቁሙ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የሣውላ ካምፓስ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ መንግሥቱ አጌና በበኩላቸው በመሎ ኮዛ ወረዳ፣ ሣውላ ከተማና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ምርምሮቹ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡ በቀጣይም አዳዲስ የቴክኖሎጂና የምርምር ሀሳቦችን ከማመንጨት አኳያ ጠንካራ ሥራዎች የሚጠበቁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡