12ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ክብረ በዓል በዩኒቨርሲቲው በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

‹‹በህገ-መንግሥታችን የደመቀ ህብረ ብሄራዊነታችን ለህዳሴያችን!›› በሚል መሪ ቃል 12ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ክብረ በዓል በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኅዳር 25/2010 ዓ/ም ተከብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በዓሉ በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተውን የህዝቦች አንድነት ይበልጥ በማጠናከር ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እሴቶቻቸውንና ባህላቸውን እንዲለዋወጡ በማድረግ በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነትና ውበት ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልፀዋል፡፡ በዓሉን በዩኒቨርሲቲው መከበሩ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ፣ ህገ-መንግሥቱን መሠረት ላደረገ የአካዳሚክ ነፃነት እውን መሆን እና ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ጉልህ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል፡፡

እንደ ፕሬዝደንቱ ገለፃ ያለንበት ዘመን የሀገራችን ብሄር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በማንነታቸው በመኩራት ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና ሌሎች ማኅበራዊ እሴቶቻቸውን በማሳደግ በመከባበርና በመፈቃቀር ላይ የተመሠረተ ጠንካራ አንድነት የፈጠሩበት፣ በኢኮኖሚ የበለፀገች ሀገር ለመሆን የተሻለ ጎዳና የተዘረጋበት፣ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ጨምሮ የተለያዩ ግዙፍ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ የሚገኙበት እና የትምህርት ተቋማት በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፉበት ጊዜ በመሆኑ በርካታ ዜጎች የትምህርትና የሥራ ዕድልን አግኝተው ከሀገሪቱ ልማት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አሁን የደረሰበት ደረጃ የዚህ ዕድገት ውጤት ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲው መንግሥትና ማህበረሰቡ የሚጠብቀውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ከተማሪዎች፣ መምህራን፣ ሠራተኞችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በቅንጅት ለመሥራት የሚተጋ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር መልካሙ ማዳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተማሪዎች መገኛ በመሆኑ ህገ-መንግሥቱ ምን ያህል በተግባር እንደዋለ፣ ተማሪዎች ስለ ህገ-መንግሥቱ ያላቸው እውቀት፣ የብሄር ብሔረሰብ አመለካከታቸውና ተቻችሎ የመኖር እሴቶች ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊታዩ የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በበዓል አከባበሩ የፓናል ውይይት፣ የጥያቄና መልስ ውድድር፣ በተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ባህላዊ አልባሳት የደመቁ ጭፈራዎችና ሌሎች አዝናኝና አስተማሪ ዝግጅቶች ቀርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ክብረ በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች አስተናጋጅነት የተካሄደ ሲሆን ዘንድሮ በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰመራ ከተማ ይከበራል፡፡