ለእንስሳት መኖ በቂ ትኩረት መስጠት አርሶ አደሩ በወተት ምርት ተጠቃሚ እንዲሆን እንደሚያስችለው ተገለፀ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት የወተት ምርትን በማሻሻል ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በጨንቻ ወረዳ በዶኮ ሻዩ ቀበሌ ያቋቋመውን የእንስሳት መኖ ልማት ፕሮጀክት ጣቢያ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃጸም ለመመልከት ኅዳር 18/2010 ዓ.ም በጣቢያው ጉብኝት አድርጓል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የእንስሳት መኖዎች አመራረትና የእንስሳት አመጋገብ ዘዴዎችን በሚገባ እንዲረዳ፣ የወተት ምርት በመጨመር ኅብረተሰቡ በቂ ወተትና የወተት ተዋፅኦዎችን እንዲጠቀምና ለገበያ እንዲያቀርብ፣ የእንስሳት መኖ ጣቢያዎችን በማቋቋምና በአርሶ አደሩ ማሳ መኖ እንዲያለማ ማስቻል እንዲሁም የወተት አምራቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር በማደራጀት ወተትና የወተት ተዋፅኦ ግብይትን መደገፍ የጉብኝቱ ዝርዝር ዓላማዎች ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ከሰጣቸው 21 ሞዴል አርሶ አደሮች 13ቱ የእንስሳት መኖ ልማት ፕሮጀክት ሥራ አንዲጎበኙ አድርጓል፡፡ የመኖ ልማት ፕሮጀክቱ 14 ዓይነት የመኖ ችግኝ ዝርያዎች ሲኖሩት የጓያ፣ ለስላሳውና ከርዳዳው የዳሾ እና የሲናር ችግኞች ለመኖነት እየደረሱ ይገኛሉ፡፡ አርሶ አደሮቹ የማሳ ውስጥ ኩሬ በማዘጋጀት በባህላዊ የቀርከሃ ውሃ ማጠጫ አማካኝነት ወደ ማሳዎች ስበዉ በማድረስ ከሩቅ አካባቢ ውሃ ለማመላለስ የሚያወጡትን ጊዜና ጉልበት በእጅጉ አንዲቀንሱ አድርጓቸዋል፡፡

ሞዴል አርሶ አደር ፋታሸ ፋሻ ባህላዊው የውሃ ማጠጫ ቀርከሃ በዘመናዊ የውሃ መሳቢያ ማሽን ቢለወጥ የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ተናግራለች፡፡ ሞዴል አርሶ አደሮችም የእርሷን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ የወረዳዉ ግብርና ባለሙያና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወ/ሮ አስናቀች ታከለ የጓያ ዘር መወደድ የጓያ ዝርያዎችን ለሌሎች አርሶ አደሮች ለማድረስ ተግዳሮት በመፍጠሩ አርሶ አደሮቹን በተፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ግብርና ሣይንስ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት አስተባባሪ ዶ/ር ምናለ ጌታቸው በበኩላቸው የወተት ምርትን ለመጨመር የጨንቻ አየር ሁኔታ ተመራጭ በመሆኑ አርሶ አደሩ ዘመናዊ የእንስሳት መኖ ችግኝ በማሳው በስፋት መጠቀም እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በጉብኝቱ የዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎችና አመራሮች፣ የተመረጡ ሞዴል አርሶ አደሮችና የወረዳው የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡