የ IUC ፕሮጀክት ፅ/ቤት የጫሞ ሐይቅ ያለበትን አስከፊ ሁኔታ ለመታደግ የተሠሩ የምርምር ውጤቶችን በማስመልከት ሐምሌ 15/2009 ዓ/ም በጫሞ ሐይቅ ጉብኝት አካሂዷል፡፡

የዩኒቨርሲቲው እንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪና የIUC ፕሮጀክት ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ እንደገለፁት ለጫሞ ሐይቅ የሚደረገው ቁጥጥርና ጥበቃ የላላ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሐይቁ ውስጥ የሚኖሩ የዓሣ፣ የጉማሬና የአዞ ዝርያዎች ቁጥር እየተመናመነ መጥቷል፡፡ የህጋዊና ህገ-ወጥ ዓሣ አስጋሪዎች ቁጥር መበራከት፣ የአካባቢው ደን ለእርሻ ሥራ መመንጠርና አስተራረሱ ዘመናዊነትን ያልተከተለ መሆን፣ የአየር ንብረት መዛባት እና የባለድርሻ አካላት ለሐይቁ ትኩረት ሰጥቶ አለመሥራት የችግሩ መባባስ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የአባያ ሐይቅ ከጫሞ ሐይቅ ጋር ሲነፃፀር ሐይቁ በባህሪው የደፈረሰ ውሃ ያዘለ ሲሆን በውስጡ የሚገኙት አዞዎች ውሃ ውስጥ የሚመገቡት ዓሣና ነፍሳት ባለመኖራቸው ከሐይቁ በመውጣት በሰው ህይወት ላይ አደጋ ሲያደርሱ ይስተዋላሉ፡፡

ዩኒቨርሲቲው የምርምር ውጤቶችን መነሻ በማድረግ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከጫሞ ሀይቅ አንድ ስ/ኪሎ ሜትር ስፋት ክልል ውስጥ ዓሣዎች ለማራባት የሚያስችል ቦታ ለማካለል እንዲሁም በሐይቁ ላይ ለሚሠሩ ተግባራት አጋር ድርጅት የሆነው GIZ የተሰኘ የጀርመን ተራድኦ ድርጅት 2 ጀልባዎች ከነሞተራቸው ለማስመጣትእና የጥበቃ ቤት ለማስገንባት ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛል፡፡

የእርሻ ሥራዎችን ዘመናዊ አስተራረስ የተከተሉ ማድረግ፣ በሐይቁ አካባቢ እፅዋትን መትከል፣ ህገ-ወጥ አስጋሪዎች ላይ ቁጥጥር ማጠናከርና ግንዛቤ ማስጨበጥ፣  ህጋዊ አስጋሪዎች ቢሆኑም ሙሉ በሙሉ የዓሳ ዝርያዎችን ሊያጠፉ ከሚችሉ ተግባራት እንዲቆጠቡ ማስቻልና መሰል ተግባራት የሐይቁን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚረዱ የመፍትሔ አማራጮች ሲሆኑ ባለድርሻ አካላት ከዩኒቨርሲቲው ጎን በመሆን ሐይቁ ከተጋረጠበት አደጋ ሊታደጉት እንደሚገባ ዶ/ር ፋሲል ተናግረዋል፡፡

የአባያ ሐይቅ 1,139 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን የምዕራብ አባያ ወረዳው ሸፌ፣ የሁምቦ ወረዳው ሀመሳ እና የሀላባ ልዩ ወረዳው ብላቴ ወንዞች የሐይቁ ገባሮች ናቸው፡፡ የአርባ ምንጭ ዙሪያዎቹ ኩልፎና ሀሬ ወንዞች ደግሞ 316 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው የጫሞ ሐይቅ ገባሮች ናቸው፡፡