ዩኒቨርሲቲው ለጥያቄያችን በቂ ምላሽ በመስጠት ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱ የመማር ማስተማሩ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሣውላ ካምፓስ ተማሪዎች ገለፁ

የመብራት መቆራረጥ፣ በቂ የኢንተርኔት አገልግሎት አለመኖር፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት እና የማጣቀሻ መጽሐፍት አለመሟላት ከተመሠረተ አጭር ጊዜያትን ባስቆጠረው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሣውላ ካምፓስ ተማሪዎች ከዚህ ቀደም እንደ ችግር የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ካምፓሱ የራሱን ትራንስፎርመርና ጀኔሬተር በመግዛት፣ የተማሪዎች መመገቢያ፣ ቤተ-መጽሐፍት እና የተሻሉ የመማሪያ ክፍሎች በአዲስ መልክ በመገንባት እንዲሁም በቂ የመጽሐፍት ግዢና የመምህራን ቅጥር በመፈፀም ካምፓሱ ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ ጥረት ማድረጉን የሣውላ ካምፓስ ዲን አቶ ገ/መድህን ጫሜኖ ገልፀዋል፡፡ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት ሥራ በሂደት ላይ ሲሆን የንፁህ መጠጥ ውሃ ከርሰ ምድር ቁፋሮ እና የኮሚዩኒኬሽንና ሚዲያ ጥናት ትምህርት ክፍል የላቦራቶሪ ግንባታ እና የኢንተርኔት ዝርጋታ በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ሥራዎች ናቸው፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በእውቀትና በክህሎት ብቁ ሆነው እንዲወጡ ብቃት ያላቸውን መምራንና በቂ ግብዓት ማሟላት እንዲሁም ምቹ የማስተማሪያ ቦታ ማዘጋጀት ያስፈልጋል ያሉት ዲኑ ካምፓሱ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የነበሩበትን ክፍተቶች ለማሟላት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

የሦስተኛ ዓመት የኮሚዩኒኬሽንና ሚዲያ ጥናት ተማሪ ቃል ኪዳን ማቴዎስና ተማሪ መቅደስ ለማ እንዲሁም የሦስተኛ ዓመት የሎጂስቲክስና ሰፕላይ ማኔጅመንት ተማሪ ያለለትአወቀ ኃይሌ በአስተያየቶቻቸው ካምፓሱ የነበሩበትን ክፍተቶች በመለየት በዘላቂነት ለመፍታትና ለመማር ማስተማር ሥራ አጋዥ የሆኑ ግብዓቶችን ለማሟላት የሚያደርጋቸው ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

ሣውላ ካምፓስ በዘንድሮው ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ 137 ተማሪዎችን እንደሚያስመርቅ ይጠበቃል፡፡