‹‹አሁንም ትኩረት ለኤች አይቪ/ኤድስ መከላከል!›› በሚል መሪ ቃል 30ኛው ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን በዓል ተከበረ

በዩኒቨርሲቲው ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት፣ የሥርዓተ ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፣ የጋሞ ጎፋ ዞን ጤና መምሪያ እና የአርባ ምንጭ ከተማ ጤና ጽ/ቤት በጋራ በመተባበር "አሁንም ትኩረት ለኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከል!!" በሚል መሪ ቃል 30ኛውን ዓለም ዓቀፍ የኤድስ ቀን እና 27ኛውን ዓለም አቀፍ የነጭ ሪባን ቀን በፓናል ውይይት፣ በሥነ-ጽሁፍ፣ ሻማ በማብራት፣ በኤች አይ ቪ/ኤድስ ምክንያት ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም በሌሎች አዝናኝና አስተማሪ ፕሮግራሞች ከኅዳር 20-23/2010 ዓ.ም በድምቀት ተከብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በዓሉ ሲከበር መዘናጋትን በመስበር ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መታደግ እንዲቻል እና በተለይ ዩኒቨርሲቲው በሚገኝበት አካባቢ ለበሽታው መስፋፋት ምክንያት የሆኑትን ሺሻ፣ ጫት እና ጭፈራ ቤቶች እንዲሁም ወጣት ሴቶችን ላልተገባ ድርጊት የሚገፋፉ ደላሎች ላይ  እርምጃ ለመውሰድ ከሚመለከታቸው አካላት የተወጣጣ ግብረኃይል ተቋቁሞ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ማስገንዘቢያ መሆኑን የሁሉ ዓቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ዓለሙ ገልፀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በተለይ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለው መዘናጋት የቫይረሱን ስርጭት የሚያባብስ እና አምራችና ጤናማ ዜጋን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት የሚፈታተን በመሆኑ የቫይረሱን ስርጭት የሚያባብሱ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማካሄድ ስርጭቱን ለመግታት በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡ በዓሉ ሲከበር የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በቁርጠኝነት መቆምና በቫይረሱ ምክንያት የሚደርሱ ቀውሶችን በጋራ መመከት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን የኤች አይ ቪ/ኤድስ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ኃላፊ አቶ ዋልታ ንጉስ በበኩላቸው የአርባ ምንጭ ከተማ ካለው ስጋት አንፃር በፌዴራልና በክልል መዋቅሮች በቅንጅት በመሥራት የበሽታውን ስርጭት መቀነስና መግታት የሁሉም ድርሻ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በዓሉን አስመልክቶ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ከጤና ሣይንስ ኮሌጅና ከሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በተጋበዙት መ/ርት ስንታየሁ አበበና አቶ መሰለ መርጊያ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት ያለበት ደረጃ እና የነጭ ሪባን በዓል አከባበር ምንነትና ዓላማው ላይ የውይይት መነሻ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡ በመነሻ ሰነዶቹ እንደተመለከተው ቸልተኝነት፣ የግንዛቤ ማነስ፣ የሴተኛ አዳሪዎች ቁጥር መጨመር፣ የሺሻና ጫት ቤቶች መስፋፋት፣ የኢኮኖሚ ችግር፣ የአቻ ግፊትና መሰል ምክንያቶች የቫይረሱ ስርጭት ከወትሮው እንዲባባስ የሚያደርጉ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

በኤች አይ ቪ /ኤድስ ዙሪያ ግንዛቤ ማስፋት፣ ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞችና ሌሎች ወገኖች ድጋፍ መስጠት፣ የተማሪዎችን ሁኔታ መከታተልና ከአላስፈላጊ የውሎና መዝናኛ ቦታዎች እንዲታቀቡ የተጠናከረ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ፣ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት የምሽት ጭፈራ ቤቶችና የሺሻና ጫት ቤቶች ዙሪያ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲሰፍን መሥራት እንዲሁም ሥርጭቱን ለመግታት ሁሉ አቀፍ ግንዛቤ መፍጠር ከዩኒቨርሲቲው የሚጠበቁ ሥራዎች መሆናቸውን ተሳታፊዎች በአስተያየታቸው ጠቁመዋል፡፡

በበዓሉ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና አመራሮች፣ የዞንና የከተማ አመራር አካላት፣ የት/ቤቶች ር/መምህራን፣ የሐይማኖት መሪዎች እና ሌሎችም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡