ዩኒቨርሲቲው ታህሳስ 7/2010 ዓ/ም 83 የህክምና ዶክተሮችን አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 59ኙ ወንዶች ሲሆኑ 24ቱ ሴቶች ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ተመራቂዎቹ በተመረቁበት የህክምና ሙያ ሙሉ አቅማቸውን በመጠቀም ለህብረተሰቡ ጤና መሻሻል በመንግሥት በኩል እየተደረገ ላለው ርብርብ ስኬታማነት ታላቅ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሀገራችን ለ2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸዉ ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ በምታደርገዉ ርብርብ በሰዉ ሀብት ልማት የዛሬዎቹ ምሩቃን የጎላ ድርሻ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ የትምህርት ፕሮግራሞች ለሀገሪቱ እድገትና ለኑሮ መሻሻል ጉልህ ሚና አላቸው ያሉት ፕሬዝደንቱ ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ፣ ቴክኖሎጂን በማላመድና ወደ ህብረተሰቡ በማሸጋገር አበረታች እንቅስቃሴዎች እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

የደቡብ ብ/ብ/ህ/ክልላዊ መንግሥት ጤና ቢሮ ኃላፊና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር አብርሃም አላኖ በበኩላቸው የጤና ልማት ሀገሪቱ ትኩረት ከሰጠችው የማህበራዊ ልማት መስኮች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው የጤና መረጃ ተዓማኒነት ጉድለት፣ የሀሰት ሪፖርት መበራከት፣ የጤና ባለሙያዎች የሙያ ሥነ-ምግባር በሚፈቅደው አግባብ ያለመጓዝና መሰል ጉዳዮች የዘርፉ ፈተናዎች በመሆናቸው ተመራቂ ተማሪዎች ሙያዊ ሥነ-ምግባርን ተከትለው ሀገርና ወገናቸውን እንዲጠቅሙ አሳስበዋል፡፡

የክልሉን የጤና መረጃ አስመልከቶ ኃላፊው ሲያብራሩ በክልሉ 716 የጤና ጣቢያዎች፣ 3,848 የጤና ኬላዎች፣ 64 ሆስፒታሎች እና በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ የጤና ተቋማት በመገንባታቸው የጤና አገልግሎት ሽፋኑ ከ95 በመቶ በላይ ሊደርስ ችሏል፡፡

ከተመራቂዎቹ መካከል ዶ/ር አሽራፍ ጩሜቶ 3.6 በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆን ዶ/ር ፍረወይኒ ፍስሃፅዮን 3.43 በማምጣት ከሴት ምሩቃን በአብላጫ ውጤት የማዕረግ ተሸላሚ ሆናለች፡፡

አድካሚውንና በፈተናዎች የታጀበውን የትምህርት ዓለም አጠናቀን ለዚህ ቀን በመብቃታችን ደስታ ተሰምቶኛል ያለው ተመራቂ ዶ/ር አሽራፍ በጤና እጦት ምክንያት የሚሰቃዩ ወገኖችን መርዳት ብሎም በትምህርት ያገኘነውን እውቀትና ክህሎት በማዳበር ሀገራችን የምትጠብቅብንን ሁሉ ማድረግ ቀጣዩ ትኩረት የምንሰጠው የቤት ሥራችን ነው ብሏል፡፡

ተመራቂ ዶ/ር ፍረወይኒ በበኩሏ ሴቶች በሀገራቸው ልማት አስተዋፅዖ ሊያበረክቱ በሚችሉበት በዚህ ወቅት በሴትነቴ ለዚህ ጅምር ውጤት መብቃቴ የሚያበረታታኝ ነው ብላለች፡፡ የህክምና ሙያ የሚጠይቀውን ሥነ-ምግባር በመጠበቅ ለሀገሯ የተቻላትን ሁሉ እንደምታደርግም ተናግራለች፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ1976 ዓ/ም በውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትነት ተመስርቶ በ1996 ወደ ዩኒቨርሲቲ ካደገ ወዲህ ከ41 ሺህ በላይ ምሁራንን ያፈራ ተቋም ሲሆን በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ላይም ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡