በሣውላ ከተማ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ግንዛቤ ማስጨበጫ የፓናል ውይይት ተካሄደ

የዩኒቨርሲቲው ሣውላ ካምፓስ ከሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ቡድን ጋር በመተባበር በኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ ታህሳስ 5/2010 ዓ.ም በሣውላ ከተማ የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡ በዕለቱ ከዚህ በፊት በከተማው ሲረዱ ከነበሩ 10 ተማሪዎች በተጨማሪ ለ20 ወላጅ አጥና አቅመ ደካማ ህፃናት ተማሪዎች ሙሉ የትምህርት መርጃና ሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የፕሮግራሙ ዓላማ “አሁንም  ትኩረት ለኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከል!!” በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ ለ30ኛ ጊዜ የተከበረውን የዓለም የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን ምክንያት በማድረግ በዞኑ በበሽታው ስርጭት በዋናነት ከሚጠቀሱና አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከሚገኙ ከተሞች አንዱና ዋነኛ በሆነው ሣውላ ከተማ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ለበሽታው መንስኤ በሆኑ ችግሮች ዙሪያ በመወያየት በሽታውን መቆጣጠርና መከላከል እንዲቻል የመፍትሄ ሀሳቦች ማቅረብ ነው፡፡

የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት የማህበረሰቡ መዘናጋት ታክሎበት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ በግለሰብም ሆነ በሀገር ደረጃ አያሌ ችግሮችን እያስከተለ መሆኑን የሣውላ ካምፓስ ዲን አቶ ገ/መድህን ጫሜኖ ገልጸዋል፡፡ በኃላፊነት በመንቀሳቀስ፣ አጋላጭ ሁኔታዎችንና ቦታዎችን በመለየትና በመቆጣጠር እንዲሁም የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት የበሽታውን ስርጭት መቀነስና መግታት ይቻላልም ብለዋል፡፡

ሁሉም በቁጭትና በባለቤትነት ስሜት ቢነሳሳ በሽታው የማይገታበት ምክንያት አይኖርም ያሉት የሣውላ ከተማ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አያሌው እርገጤ በበኩላቸው በሽታው ለልማታችን እንቅፋት እንዳይፈጥር በንቃት በመሳተፍ ተጋላጭ የሆነውን የማህበረሰብ ክፍል የመደገፍና የማብቃት ሥራ በየደረጃው በእቅድ መመራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በሁሉአቀፍ ዳይሬክቶሬት የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ቡድን ባለሙያ አቶ መርክነህ መኩሪያ ኤች አይ ቪ/ኤድስን በተመለከተ በዓለም፣ በአህጉርና በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በዞኑ ባሉ እውነታዎች ላይ የውይይት መነሻ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡ የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎችም ዳግም የሚያንሠራራውን ቫይረስ ሥርጭት በሚያባብሱ አጋላጭ የአካባቢያቸው ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ በጥልቀት መክረው የመፍትሔ ሀሳቦችን አስቀምጠዋል፡፡

የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚደረጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ወቅት ጠብቀው ብቻ መካሄዳቸውና ትምህርትና ድጋፎች ተከታታይነት ባለው መልኩ ማህበረሰቡን አለማሳተፋቸው፣ የክበባትና የማህበረሰብ ውይይቶች መዳከም፣ ለወጣቶች ለሥራ ምቹ ሁኔታ በስፋት አለመፈጠር፣ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ መዳከም እንዲሁም በህገ ወጥ ጫት መቃሚያና የምሽት ጭፈራ ቤቶች እና  ሴተኛ አዳሪዎች ዙሪያ ጥብቅ ቁጥጥር አለመኖር በሽታው በከተማው እንደገና እዲያንሠራራ ምክንያት መሆናቸው በውይይቱ ተጠቅሷል፡፡ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ሁሉም ማህበረሰብ በመቀናጀት መሥራትና የራሱን ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ተሳታፊዎቹ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ውይይቱን በከተማው ካሉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የመጡ ተሳታፊዎች፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የሣውላ ካምፓስ አመራሮችና ተማሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተካፍለዋል፡፡