የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥነ-ህይወትና የባህል ብዝሃት ምርምር ማዕከል ተመራማሪዎች ከግብርና ሳይንስ ኮሌጅ የዕፅዋት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህራን ጋር በመተባበር በጨንቻ ወረዳ ግርጫ ኦቴ እና በዶርዜ ሆሎኦ ቀበሌያት ምርምር እያካሄዱባቸው የሚገኙ የቢራ ገብስ ዝርያዎች ምርታማነት ታህሳስ 10/2010 ዓ/ም የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የቢራ ገብስ በሀገሪቱ ደጋማ አካባቢዎች የሚበቅል ሲሆን የጋሞ ጎፋ ዞን ደጋማ ወረዳዎች ለቢራ ገብስ ምርት ተስማሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታሰባል፡፡ ነገር ግን አካባቢው በቢራ ገብስ አምራችነት የማይታወቅ በመሆኑ የምርምር ማዕከሉ ከዲታና ጨንቻ ወረዳዎች የተገኙ ስድስት በአካባቢው የተሻሉ የጠላ ገብስ ዝርያዎችና ከቁልምሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የተገኙ ስድስት የቢራ ገብስ ዝርያዎች በአጠቃላይ አስራ ሁለት ዝርያዎች ላይ ምርምር እያካሄደ ነው፡፡

የማዕከሉ ተመራማሪ አቶ ተመስገን ዲንጋሞ እንደገለፁት ምርምር ከሚደርግባቸው ነባር የአካባቢው ዝርያዎች አንዱ የሆነው ቦቴ በጥቂት ቦታ ከፍተኛ ምርት የሚያስገኝ በመሆኑ የአካባቢውን ህብረተሰብ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር የጎላ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ የቢራ ገብስን በማምረት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ አርሶ አደሮች በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተመራማሪው ጠቅሰው ይህንን አርአያነት ወደ አካባቢያችን በማምጣት አርሶ አደሩ በማሳው ላይ በምርምር የተደገፈ ምርት አምርቶ ተጠቃሚ እንዲሆን እንሠራለን ብለዋል፡፡

የኦቴ ቀበሌ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አምባ አካሉ ለሙከራ የመጡት ባሀቲ (Bahati)ና ኢቦን (Ibon)የቢራ ገብስ ዝርያዎች ጥሩ ውጤት ያሳዩ መሆኑን ተናግረው በአካባቢው ለምግብነት የሚውለው ካዎ ባንጋ የሚባለው የገብስ ዝርያ ጥናት ተደርጎበት ለቢራ ጠመቃ የሚውል ቢሆን ከፍተኛ ውጤት የሚያስገኝ ነው ብለዋል፡፡

የጨንቻ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ አልቦ በበኩላቸው የምርምር ውጤቱን ተከትሎ በተቀናጀ መልኩ በመሥራት ከ4,000 በላይ ሄክታር መሬት ላይ ገብስ ለማምረት መታቀዱን ገልፀዋል፡፡

አርሶ አደር ጭዳ ጩፋቆ ባዩት ነገር መደሰታቸውን ተናግረው ወደፊት በሰፊው ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡

የሥነ-ሕይወትና የባህል ብዝሃነት ምርምር ማዕከል የአካባቢውን ብዝሃ ሕይወትና የባህል ብዝሃነትን መጠበቅ፣ መንከባከብ ብሎም በዘላቂነት መጠቀም እንዲቻል ምርምሮችን በማካሄድ ለህበረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ማዕከሉ በብዝሃ ህይወትና በባህል ብዝሃነት ላይ ችግር ፊቺ ጥናትና ምርምር በማካሄድ በ2012 ዓ/ም በሀገሪቱ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ አቻ የምርምር ማዕከላት አንዱ ለመሆን አቅዶ እየሠራ ነው፡፡