በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ግቢ የተሠሩ የተለያዩ የግቢ ውበት ፕሮጀክቶች ተመረቁ

የሥነ-ህንፃና ከተማ ፕላን እና የሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍሎች መምህራን በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ግቢ የሠሯቸው የተለያዩ የግቢ ውበት ፕሮጀክቶች ኅዳር 15/2010 ዓ/ም ተመርቀዋል፡፡ ለፕሮጀክቶቹ መሳካት የጎላ ሚና ለተጫወቱ ግለሰቦች የምስክር ወረቀትና የልዩ ሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

ፕሮጀክቱ 4 የህዝብ መናፈሻ፣ 1 መፀዳጃ ቤት፣ የተማሪዎች ልብስ ማጠቢያ እንዲሁም የምግብ ቤት ሠራተኞች የዕቃ ማጠቢያ እና የእጅ መታጠቢያ ቧንቧ መስመር ጥገናን ያቀፈ ነው፡፡ በተጨማሪም አገልግሎት የማይሰጡ አንዳንድ ቤቶች ተጠግነዉ ለመምህራን መኖሪያነት እንዲውሉ የተደረገ ሲሆን ለረጂም ጊዜ ጣሪያቸው የሚያፈሱ የተማሪዎች መኝታ ክፍሎችና የመማሪያ ክፍል ኮሪደሮች ጥገናም የፕሮጀክቱ አካል ናቸው፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ በመክፈቻ ንግግራቸው ይህን መሰል የተለያዩ ሳቢ ሥፍራዎች በብዛት መሠራታቸዉ የግቢዉን ገጽታ በበጎ መልኩ የሚቀይሩ ናቸው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠዉ ዳርዛ የተመለከቷቸው የተለያዩ የግቢው ህንፃዎች እድሳትና ማራኪ ሥፍራዎች  የተለየ ስሜት እንደፈጠሩባቸው ገልጸዋል፡፡ የግቢዉን ችግር እንደራሳቸው በመረዳት በራስ ተነሳሽነት ሌሎች መምህራንን በማስተባበር ለፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከታቸው እንደ መምህርት ታሪኳ ወ/መድህን ያሉ አርአያ የሆኑ ሰዎች ሊበረታቱና በቀጣይነት ሊደገፉ ይገባል ብለዋል፡፡ ለተማሪዎችም በየክፍላቸው አቅራቢያ ይህ ሳቢ ቦታ መፈጠሩ ከማስደሰቱም ባለፈ ለሌላ ፈጠራ ሥራ እንደሚያነሳሳቸዉ ፕሬዝደንቱ አስገንዝበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል በበኩላቸው የግቢ ውበት ሥራ እስከዛሬ ትኩረት ቢያገኝ የዩኒቨርሲቲውን ገጽታ የበለጠ አጉልቶ ያሳይ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ በተሰሩት የፕሮጀክት ሥራዎች የግቢዉ መምህራን መደሰታቸውን ተናግረው በቀጣይም ሌሎች መምህራንን በማሳተፍ የተለያዩ የግቢ ውበት ሥራዎች ተሰርተው ግቢው ማራኪ የትምህርት መስጫ ማዕከል እንደሚሆን ከወዲሁ አሳይቶናል ብለዋል፡፡

ሥራዎቹ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የረጅም ጊዜ ጥያቄዎች እንደነበሩ ያስረዱት የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ም/ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የፕሮጀክቱ ማኔጀር መ/ርት ታሪኳ ወ/መድህን በተለይ  የተማሪ ምግብ ቤት ሠራተኞች የእቃ ማጠቢያና የእጅ መታጠቢያ ውሃ በፈለጉት መጠን ማግኘት ፈተና ሆኖባቸዉ ቆይቷል ብለዋል፡፡  መምህርቷ ወደ ኃላፊነት ከመምጣታቸዉ  በፊት እነዚህን ሥራዎች ለማከናወን በእጅጉ ሲቆጩ እንደነበር አስታውሰው ተጨማሪ የውበት ቦታዎችን በግቢዉ ለመፍጠር በማሰብ ፕሮፖዛሉ በመምህራን ሲቀርብ በደስታ መቀበላቸውን አብራርተዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች በእቅዱ ደስተኛ በመሆናቸውና  ሴኔቱ ተወያይቶ በመወሰኑ በቀጥታ ወደ ሥራዉ ሊገቡ እንደቻሉ ገልፀዋል፡፡

የኮሚቴ መዋቀርና ለእያንዳንዱ ፕሮጀክት ሳይት የራሱ ተቆጣጣሪ መኖር ለፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ ከፍተኛዉን ድርሻ እንደተወጣ ማኔጀሯ ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክት ንድፉን በመቅረጽና በማስፈጸም መ/ርት ታሪኳ ወ/መድህን፣ መምህር ግዛዉ ፍቅሬ፣ መምህር መሳፍንት ውሂብ፣ መምህር ጥላሁን ካሳ፣ መምህር ገዛኸኝ ዘርይሁን እና መምህር አቤል ሁነኛዉ ተሳትፈዋል፡፡ ሥራው በዋናነት የግንባታ ቁሳቁስ ግዢና የቀን ሠራተኛ ወጪ ብቻ የጠየቀ ሲሆን ለጨረታ ቢቀርብ ከ 700 ሺህ ብር በላይ ተጨማሪ ወጪ ሊያስወጣ እንደሚችል ተገልጿል፡፡