በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገ/ማ/ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት በዓለም ለ26ኛ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ25ኛ ጊዜ ‹‹ሁሉን አቀፍ ጠንካራና ዘላቂ ማህበረሰብ እንገንባ!’’ በሚል መሪ ቃል የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓል ኅዳር 24/2010 ዓ/ም በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ፕሬዝደንቱ ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በሌሎች የሀገራችን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካል ጉዳተኞች የትምህርት ተሳትፎና ውጤታማነት ከዓመት ወደ ዓመት እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለዉ የኢኮኖሚ እድገት ሙሉ እና ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል መንግሥት ከቀረጻቸዉ ፖሊሲዎች እና ከነደፋቸው ስትራቴጂዎች ጎን ለጎን ሁሉን አቀፍ፣ ጠንካራና ዘላቂ ማህበረሰብ መገንባት ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን ተማሪዎች በዕዉቀት በክህሎት እና በሥነ-ምግባር የታነጹ መልካም ዜጋ እንዲሆኑ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርፆ በመስራት ላይ መሆኑን ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

የተ/አገ/ማ/ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አየልኝ ጎታ በበኩላቸው የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ላቅ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ እንዳሉ ጠቁመው ቢዘህም ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አካባቢ በመፍጠር እንደማንኛዉም ተማሪ አካል ጉዳታቸዉ ሳያግዳቸዉ በትምህርታቸዉ ውጤታማ እንዲሆኑ የሁሉም የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንደማይለያቸው ተናግረዋል፡፡

በበዓሉ ላይ መ/ር ሙሉቀን ተስፋዬ አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ በዓለምና በሀገር አቀፍ ማዕቀፎች እና በዩኒቨርሲቲው የሚሰጡ አገልግሎቶች ዙሪያ ባሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ የውይይት መነሻ የዳሰሳ ጥናት አቅርበዋል፡፡ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የትምህርት አካባቢ ለመፍጠር በሚደረገው ሂደት ዩኒቨርሲቲው የአገልግሎት መስጫ ሁኔታዎች፣ የአቅም ግንባታና የአመራርነት ሚናቸውን ለማጎልበት እያደረገ ያለውን ሂደት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡