በዩኒቨርሲቲው ሀሰተኛ የትምህርትና የሥራ ማስረጃዎች የማጣራት ሥራ ተጀመረ

የዩኒቨርሲቲው የሀሰተኛ ማስረጃ አጣሪ ኮሚቴ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ታህሳስ 16/2010 ዓ/ም ውይይት አድርጓል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚቀጠረው የሰው ኃይል በትምህርት ዝግጅትም ሆነ በሥራ ልምድ ተፈላጊውን ችሎታ አሟልቶ መገኘት ያለበት ሲሆን በተቋም ውስጥ የሚካሄድ የደረጃ እድገትም በተመሳሳይ መልኩ ተፈላጊውን ችሎታን ማዕከል አድርጎ የሚፈፀም ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ የሀሰተኛ ማስረጃዎችን በማቅረብ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚደረግ ማንኛውም ተግባር የልማትና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ሥራ እንቅፋት በመሆኑ ሊታረም ይገባዋል ሲሉ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል፡፡

በፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች በማገልገል ላይ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች በማስረጃነት ያቀረቧቸው የትምህርት፣ የሥራ ልምድ፣ የብቃት ማረጋገጫ (COC)፣ የመንጃ ፈቃድ ወዘተ ማስረጃዎችን ትክክለኛነት በማጣራት ፐብሊክ ሰርቪሱ ከዚህ መሰል የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የፀዳ መሆኑን እንዲሁም የሠራተኛ ስምሪት በትክክለኛ ማስረጃ መፈፀሙን በማረጋገጥ ውጤታማ የተልዕኮ አፈጻጸም እንዲኖር ለማስቻል ሀሰተኛ ማስረጃዎችን ማጣራት ማስፈለጉን የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ዳባ ገልጸዋል፡፡

ሀሰተኛ ማስረጃዎችን የማጣራት ሥራ በዩኒቨርሲቲው በይፋ መጀመሩን በመግለጽ በጉዳዩ የተሳተፉ ግለሰቦች ከታህሳስ 16 እስከ ጥር 7/2010 ዓ/ም ድረስ ራሳቸውን እንዲያጋልጡ ኮሚቴው ጥሪውን አቅርቧል፡፡ ራሳቸውን የሚያጋልጡ ግለሰቦች ቅጣት የማይጣልባቸው ሲሆን ካሉበት የሥራ መደብ ተነስተው ወደሚመጥናቸው መደብ ዝውውር እንደሚደረግላቸው ተገልጿል፡፡ ራስን ለማጋለጥ የተጣለው የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቅ ሌሎች ሠራተኞች በሀሰተኛ ማስረጃ የሚጠቀሙ ግለሰቦችን በመጠቆም የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል፡፡