የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል እና ከጋሞ ጎፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ጋር በመተባበር በአርባ ምንጭ ከተማ ከሚገኙት የሲአስ እና ነጭ ሳር አስጎብኚ ማህበራት ለተወጣጡ 15 የእንግዳ አስጎብኚዎች (Tour guides) ከታህሳስ 9 - 11/2010 ዓ/ም ለ3 ተከታታይ ቀናት በሙያው ህግና አተገባበር ላይ ያተኮረ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የሥልጠናው ዓላማ በአርባ ምንጭ ከተማ የቱሪስት ፍሰቱን ያህል የአስጎብኚዎቹ አገልግሎት ጥራት እንዲኖረው ማገዝ እና የቱሪስቶችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ በአስጎብኚዎች በኩል የሚስተዋለውን የክህሎት ክፍተት መቅረፍ መሆኑን የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማህበረሰብ አገ/ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ርት ትዕግስት ኃይሌ ገልፀዋል፡፡

ስልጠናውን የሰጡት የቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት ት/ክፍል መ/ር ንጉሴ ጥሩነህ አንድ እንግዳ አስጎብኚ በዘርፉ  የተመረቀ፣ የተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ መስህቦችን ለጎብኚዎች በሚገባ መግለጽ የሚችል፣ ሁለትና  ከዚያ በላይ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን የሚያውቅ እና የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ዕውቀት ያለው ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማህበረሰቡን ማንነትና ምንነት እንዲሁም ትውፊቶችን፣ ልማዶችንና አባባሎችን በማስረጃ እያስደገፈ የሚያቀርብና የመስህቡን ምሉዕነት የሚያሳይ እንዲሁም ጎብኚውን በሚገባ መምራት የሚችል መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ጎብኚዎች ተገቢውን አገልግሎት በአግባቡ ካገኙና በመስተንግዶ ከተደሰቱ ሌሎች ጎብኚዎችን ወደ ሀገራችን በማምጣት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑን አሰልጣኙ አብራርተዋል፡፡

የትምህርት ክፍሉ መምህር  ጋሻው  ጌታሁን በበኩላቸው አንድ አስጎብኚ  ቱሪስት ፊት የሚቀርበው ራሱን ብቻ ወክሎ ሳይሆን የወጣበትንና የሚያስተዋውቀውን ማህበረሰብ አምሳያ ይዞ በመሆኑ እንደ አምባሳደር የሚቆጠር መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም ስብዕናው የተሟላና ማህበረሰቡን ሙሉ ለሙሉ የሚወክል እንዲሁም ማህበረሰቡን የሚያስተዋውቅ ግለሰባዊ ብቃት ያለው፣ ሙያው የሚጠይቀውን ሥነ - ምግባር ያሟላ፣ ሰዓት አክባሪና  ታማኝ  መሆን አለበት ብለዋል፡፡

አስጎብኚዎቹ ጉዞዎችን እንዴት ማቀድ እንዳለባቸውና ሊካተቱ የሚገቡ ጉዳዮች፣ ጎብኚዎች ለጉብኝት መጥተው እስኪመለሱ ያሉ ቅደም ተከተሎች እንዲሁም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶችን አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

ስልጠናው በርካታ ጥቅሞች ያለውና ከሥራው ጋር ተያይዞ ያለውን ክፍተት የሚሞላ ከመሆኑም ባሻገር ሀገር ሊጎበኙ የሚመጡ እንግዶችን እንዴት እንደሚያስተናግዱ መረጃ እንዲያገኙ ያስቻላቸው መሆኑን ሰልጣኞች በአስተያየታቸው ገልፀው ስልጠናው ቀጣይነት ቢኖረው መልካም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡