የበጎ አድራጎት ክበብ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም አዘጋጀ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የበጎ አድራጎት ክበብ "አንድ ዲፓርትመንት አንድ ልጅ ማሳደግ ይችላል!" በሚል መሪ ቃል ጥቅምት 18/2010 ዓ.ም ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም አዘጋጅቷል፡፡ በፕሮግራሙ የክበቡ ዓመታዊ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ክበቡ ለ12 አቅመ ደካማ ተማሪዎች ድጋፍ እያደረገ ሲሆን 8ቱን በ1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች እንዲሁም 4ቱን ደግሞ በዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

በ1993 ዓ.ም በክበቡ ተረጂነት የታቀፈው ተማሪ እስክንድር ዋሽኬ ከኬጂ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ቁሳቁሶችና የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን ተናግሯል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ የሆነው እስክንድር የመጓጓዣ ወጪውንና የትምህርት ቁሳቁሶችን ክበቡ ያሟላለት ሲሆን የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እስኪያጠናቅቅ ድረስ የሚደረግለት ድጋፍ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ይህ ድጋፍ ወደፊት ሌሎች ድጋፍ ፈላጊ ተማሪዎችን በአቅሜ እንድረዳ በጎ ሥነ-ልቦናዊ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል ብሏል፡፡

በተመሳሳይ ተማሪ ርብቃ አየለ ወላጅ አጥ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ከ2003 ዓ/ም ጀምሮ በክበቡ እየተረዳች ነው፡፡ ተማሪ ርብቃ ክበቡ ለሚያደርግላት ድጋፍና ክትትል ምስጋናዋን ያቀረበች ሲሆን ወደ ፊት ወላጅ አጥና አቅመ ደካማ ልጆችን ለመርዳት እንደምትፈልግ ተናግራለች፡፡

የበጎ አድራጎት ክበብ ፕሬዝደንት ተማሪ ፍሬው ካሳሁን እንደተናገረው ክበቡ እየተንቀሳቀሰ ያለው ከዚህ ቀደም በተሰበሰበ ገንዘብ ሲሆን ሥራውን ለማስቀጠል አስጊ ሁኔታ ላይ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ገቢ ለማሰባሰብ የዩኒቨርሲቲውንና የከተማውን ማህበረሰብ በማሳተፍ እና ታዋቂ አትሌቶችና አርቲስቶችን በመጋበዝ ታላቁን የበጎ አድራጎት ሩጫ እና ኮንሰርት ለማዘጋጀት ታቅዷል ብሏል፡፡