የሠራተኞችን ድልድል የሚፈፅሙ የሠራተኛ ተወካዮች ምርጫ ተካሄደ

‹‹ለእኩል ስራ እኩል ክፍያ›› በሚል መርህ በአዲሱ የስራ ደረጃ ምዘና አወሳሰን ዘዴ/JEG/ የዩኒቨርሲቲውን የአስተዳደር ሰራተኞች ለመደልደል የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ታህሳስ 20/2010 ዓ/ም የሰራተኞችን ተወካይ ያቀፈ ደልዳይ ኮሚቴ ምርጫ አካሂዷል፡፡ ምርጫው የተካሄደው ከሁሉም ኮሌጆች፣ ኢንስቲትዩቶችና ዳይሬክቶሬቶች በተወጣጡ የሰራተኛ ተወካዮች ነው፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ከአምላክነሽ ደሳለኝ እንደገለፁት ውድድሩ በትምህርት ዝግጅትና በአገልግሎት ቢሆንም የሰራተኛውን ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር ሰራተኛውን ወክሎ የሚገኝ ተሳታፊ መኖሩ  ድልደላው በሚካሄድበት ወቅት አድሏዊና ኢ-ፍትሃዊ አሰራሮች እንዳይፈጠሩ ብሎም የሌሎች ኃላፊዎች ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር ያደርጋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ተመራጮቹ በስነ-ምግባር፣ በስራ አፈፃፀምና በለውጥ ስራዎች ትግበራ አርአያ የሆኑ፣ የሰራተኛውን መብት የሚያስጠብቁ፣ ከወገንተኝነትና ከአድሏዊ አሰራር የፀዱ እንዲሁም ስራውን ለማስፈፀም ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ቀደም ሲል የነበሩት 6 የስራ መደቦች ተቀይረው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከደረጃ 1 - 22 እንዲመዘኑ መደረጉን የተናገሩት ዳይሬክተሯ በዚህም መሰረት በዩኒቨርሲቲው የሚከናወኑ ተግባራት ተመዝነው ከ1 - 18 ደረጃ የወጣላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በቀጣይም የስራ ደረጃ ምዘና አወሳሰን ዘዴ/JEG/ ምንነትና የስራ ድልድሉን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ይኖራል ብለዋል፡፡

በድልድሉ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት የሚወክሏቸው ሁለት አባላትና አንድ ሰብሳቢ እንዲሁም ሁለት የሰራተኛ ተወካዮች የሚገኙ ሲሆን የሰው ሀብት አስተዳደር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ድምፅ አልባ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡