የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳግም ተቋቋመ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መሰረት የሆነው የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በመከፈል ዳግም መቋቋሙንና በአዲስ መልክ ሥራ መጀመሩን በይፋ ለማስተዋወቅና ግቦቹ ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ታህሳስ 23/2010 ዓ/ም ፕሮግራም አዘጋጅቷል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ቀደም ሲል ሲሠራ በነበረው ላይ አዳዲስ ተግባራትን በመጨመር በዘርፉ ያለውን እምቅ ሀብት መጠቀም በሚያስችል መልኩ የሰው ኃይል በጥራት በማፍራት፣ ምርምሮችን በማከናወን እና ተወዳዳሪ በመሆን ለሀገር አስተዋጽኦ ለማበርከት ኢንስቲትዩቱ ዳግም መቋቋሙን የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል ገልፀዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱን ዳግም መከፈት  አስፈላጊነት፣ የወደፊት አቅጣጫ፣  መልካም አጋጣሚዎች፣ ተግዳሮቶች፣ በኢንስቲትዩቱ በአሁኑ ወቅት ምን ምን ተግባራት እየተከናወኑ እንዳሉ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ግንዛቤ ለመፍጠር ፕሮግራሙ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የኢንስቲትዩቱ ዳግም እውን መሆን ዩኒቨርሲቲው ቀድሞ በዘርፉ በአህጉር ደረጃ የነበረውን እውቅናና ጉልህ ተግባር በማጠናከር የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለማስቀጠል እንዲሁም በአመለካከት፣ በአስተሳሰብና በስብዕና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ወሳኝ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡ ለዚህም የመምህራን ድርሻ የላቀ በመሆኑ ለስኬቱ ማማር በቁርጠኝነት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የኢንሲቲትዩቱን ዳግም መወለድ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ፕሮግራሞችን በመቅረጽ  የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ዜጎችን በመሳብና የምሁራን ልውውጥ በማዳበር ረገድ ወቅቱ በሚፈልገው መጠን እንዲሠራ አጽንኦት ተሰጥቷል፡፡ የኢንስቲትዩቱ እውን መሆን በመማር ማስተማር፣ በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት ቀደም ሲል በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሥር  የነበረውን አሰራር ጥራት ባለው መልኩ ከማቀላጠፍ ባሻገር ለዩኒቨርሲቲው የተሻለ አቅም የሚፈጥርና እንደ ሀገር በዘርፉ ለተቀመጠው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ስኬት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም እምነት የተጣለበት ነው፡፡

በፕሮግራሙ በዘርፉ ያሉ መልካም አጋጣሚዎችና ስጋቶች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በውሃ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ካለው የገዘፈ ስም አንጻር ባለው ተቀባይነት መነሻነት ዓለም አቀፍ ውህደት መፍጠር የሚያስችል አቋም መኖሩ፣ የቀድሞ ምሩቃን በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች መገኘታቸው፣  የመንግስት ስትራቴጂክ አቅጣጫ ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱ፣ በሀገሪቱ እምቅ የውሃ ሀብት በስፋት መኖሩ፣ በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት መኖሩ፣ በዘርፉ ያለው በቂ መሰረተ ልማትና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች እንደመልካም አጋጣሚዎች ተጠቅሰዋል፡፡ በአንፃሩ የመምህራን ፍልሰት፣ የቤተ-ሙከራዎች እድሜ መግፋት፣ በዘርፉ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ መምህራንና ተመራማሪዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖርና ሌሎችም እንደ ስጋት ተነስተዋል፡፡

ተሳታፊዎች በኢንስቲትዩቱ ዳግም ምሥረታ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ሳኒቴሪና የውሃ አቅርቦት በመሳሰሉ ከውሃ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በስፋት እቅድ እንዲያዝ፣ ለነባር መምህራን ተገቢ የማትጊያ ፓኬጆች እንዲቀመጡ እንዲሁም ለዘርፉ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ይዘትን የጠበቁ የአጭርና የረጅም ጊዜ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎች እንዲመቻቹ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የውሃ ዘርፍ መምህራንና ተመራማሪዎች፣ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራንና  ሌሎችም ተሳትፈዋል፡፡