የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ከአምራች ኢንደስትሪዎች ጋር በቂ ትስስር በማድረግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ብሎም ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ ገበያ ለመወዳደር ከሚያስችላት የአቅርቦትና የጥራት ደረጃ ለማድረስ እንደሚሠራ ገለፀ፡፡

ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለፁት ዳይሬክቶሬቱ የመንግስትን ተልዕኮ ከማስፈጸም አንጻር የኢንደስትሪ ትስስር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የተማሪዎችና የመምህራን ኢንተርፕርነርሽፕ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

ዩኒቨርሲቲ እውቀት ሲያመርት ኢንደስትሪ ደግሞ የሚፈለገውን ምርት ያመርታል ያሉት ዶ/ር ቶሌራ ኢንደስትሪዎች ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር ካልፈጠሩ ምርቶች ብዛት እንጂ ተፈላጊ የጥራት ደረጃ እንደማይኖራቸው ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከአምራች ኢንደስትሪዎች ጋር ቴክኖሎጂን ያካተተ ትስስር መፍጠሩ ተማሪዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትውውቅ በማድረግ የተግባር እውቀትና የፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ከማድረጉም ባሻገር ሀገሪቱ በኢንደስትሪው ዘርፍ ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ እንድትሆን ሚናው የጎላ  ነው፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ዩኒቨርሲቲው የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ከማድረጉ በፊት ከኢንደስትሪዎች ጋር በቂ የትውውቅና የመስማማት ሥራን ማስቀደም አለበት፡፡ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ ቆዳ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ ከአቃቂ ብረታ ብረት ኢንደስትሪ፣ ከደቡብ መረጃና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ፣ ከደቡብ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ፣ ከደቡብ ስምጥ ሸለቆ ባለሥልጣን እንዲሁም ከኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ጋር ትስስር በመፍጠር ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

ዳይሬክቶሬቱ 8 ከሚደርሱ በአካባቢውና በአጎራባች ወረዳዎች የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር ትስስር በመፍጠር የተቋማቱን እውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በመጠቀም እና የማህበረሰቡን ፍላጎት በመለየት ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለማምረት የሚያስችላቸውን አቅም አሳድገው ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ የሚያደርግ ሥራ ለመሥራት ዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ዶ/ር ቶሌራ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ በዳይሬክቶሬቱ የውስጥ ግብዓት ማሟላት፣ በቂ በጀት መመደብ እንዲሁም የባለሙያና የቢሮ እጥረትን መቅረፍ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል፡፡