ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ለመፍጠር በቁርጠኝነት መታገል ይገባል

የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት የተቀናጀ ዩኒቨርሲቲ አቀፍ ስትራቴጂያዊ ዕቅድን መሰረት በማድረግ ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ለመፍጠር የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጿል፡፡

የሙስና ጉዳይ ለአንድ የሥራ ክፍል ብቻ የሚተው ባለመሆኑ እያንዳንዱ የተቋሙ ኃላፊ ሙስናን ለመዋጋት የሚረዳውን አደረጃጀት ፈጥሮ በቁርጠኝነት እንዲታገል በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት የሚመራ የሙስና መከላከልና የሥነ-ምግባር ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ዳባ ገልፀዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ሙስና የአመለካከትና የሥነ-ምግባር ችግር ባላቸው አመራሮችና ሌሎችም የሚፈጸም ረቂቅና ውስብስብ ተግባር በመሆኑ በቂ መረጃ የማግኘቱን ሂደት አስቸጋሪ ከማድረጉም ባሻገር አጥፊዎችን በተፋጠነ መልኩ በህግ የመዳኘት ሥርዓቱን የሚያስተጓጉል ነው ያሉት አቶ ዘውዱ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› የሚለውን የሙስና አስተሳሰብ በመታገል እያንዳንዱ የሥራ ክፍል አገልግሎት አሰጣጡን  በማሻሻል የተሻለ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

2,600 ለሚሆኑ አዲስ መምህራን፣ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች በሥነ-ምግባር ፅንሰ ሃሳብ ላይ ስልጠና መስጠት፣ ኦዲተሮችና የዲሲፕሊን ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች በሚያቀርቡት ሪፖርት መሠረት የሚሰጡ ውሳኔዎች ላይ በቂ ክትትል ማድረግ፣ የጥቆማና አስተያየት መስጫ ሳጥኖች በሁሉም ካምፓሶች እንዲኖሩ ማድረግ እና የሀሰተኛ ማስረጃዎች አጣሪ ኮሚቴ ማቋቋም ዳይሬክቶሬቱ ካከናወናቸው ተግባራት ጥቂቶቹ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ የተቋሙን ስትራቴጂያዊ ዕቅዶች መሠረት በማድረግ ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ ለመቅረጽና በሁሉም ካምፓሶች በሚገኙ የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሙስና መከላከልና የሥነ-ምግባር ካውንስል እንዳረጋገጠው ፋይናንስና በጀት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት፣ ቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት፣ ግዢና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት፣ ግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት፣ የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት፣ ጠቅላላ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት እና የይዞታ ልማት መገ/መሣ/አስ ዳይሬክቶሬት በዩኒቨርሲቲው ለሙስና ተጋላጭ  ከሆኑ መካከል መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡