ለአዲስ ገቢ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ስልጠና ተሰጠ

በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል አዘጋጅነት ለአዲስ ገቢ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ከኅዳር 17-ታህሳስ 22/2010 ዓ.ም ለአራት ተከታታይ እሁዶች የእንግሊዝኛ ቋንቋ እና መሠረታዊ የኮምፒዩተር ክህሎት ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ስልጠናውን 45 ወንድ እና 20 ሴት ባጠቃላይ 65 ተማሪዎች ተከታትለዋል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ አየልኝ ጎታ እንደገለፁት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎታቸው እንዲዳብርና በክፍል ትምህርት አቀባበል ላይ እንዲረዳቸው በማለም ስልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡ በሌላ በኩል የኮምፒዩተር ስልጠናው  መሠረታዊ የኮምፒዩተር ክህሎቶችን አዳብረው በክፍል ውስጥ የሚሰጧቸውን የተለያዩ የኮምፒዩተር ትምህርቶች ሳይቸገሩ እንዲከታተሉና እንዲለማመዱ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው እንዲጨምር አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡

አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ከሌላው ተማሪ ራሳቸዉን አሳንሰው ሳይመለከቱ ትምህርታቸውን በንፁህ አዕምሮ እንዲከታተሉ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የኮፒ አገልግሎቶችን በነፃ እንዲያገኙ ያደረገ ሲሆን ለእያንዳንዱ ተማሪ በወር 50 ብር ይደጎም የነበረውን ወደ 100 ብር አሳድጓል፡፡

በቀጣይም በሁሉም ካምፓሶች የሚገነቡ የመማሪያ ክፍሎች፣ መፀዳጃ ቤቶች እና ሌሎች ህንፃዎች አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ በትኩረት የሚሠራ መሆኑን አቶ አየልኝ  ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ከሚሰጣቸዉ ሴት ተማሪዎች ጋር አብረው ትምህርት የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የልዩ ድጋፍ ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ አቶ አብዮት በላይነህ ለተማሪዎቹ በየጊዜዉ ከሚሰጠው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያና የመሠረታዊ ኮምፒዩተር ክህሎት ስልጠና ጎን ለጎን በየካምፓሱ ተጨማሪ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡ በ2009 የትምህርት ዘመን ተማሪዎቹ ወደ ሃዋሳና ጂማ ዩኒቨርሲቲዎች ተጉዘው ልምድና ተሞክሮ መቅሰማቸውን አስተባባሪው ጠቅሰዋል፡፡