‹‹ሀሰተኛ ሰነዶችን በማጋለጥ የፀረ-ሙስና ትግሉን እናጠናክራለን!››

‹‹ሀሰተኛ ሰነዶችን በማጋለጥ የፀረ-ሙስና ትግሉን እናጠናክራለን!›› በሚል መሪ ቃል የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ቀን ታህሳስ 18/2010 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ለ4ኛ ጊዜ ተከብሮ ውሏል፡፡ በዓሉ ሲከበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ ጊዜ ሲሆን በሀገራችን ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ ነው፡፡ በዕለቱ የሙስና ምንነት፣ አይነቶች፣ የሚያስከትላቸዉ ጉዳቶች እንዲሁም የመልካም ሥነ-ምግባርና የዕኩይ ሥነ-ምግባር መገለጫዎች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ዳባ እንደተናገሩት በዓሉ ሲከበር ከሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ጽንሰ-ሀሳብ ጎን ለጎን ከትምህርት ሚኒስቴር በተላለፈው መሠረት በዩኒቨርሲቲው ሀሰተኛ የሥራና የትምህርት ማስረጃን የማጣራት ሥራ መጀመሩንና ሠራተኛውም ጥቆማ ማድረግ እንደሚችል ከወዲሁ ግንዛቤ ለመፍጠር ታልሞ ነው፡፡

በዓሉን ስናከብር ሁለት አበይት ዓላማዎችን አንግበን ነው ያሉት ዳይሬክተሩ የመጀመሪያው በፈዴራል አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች በማገልገል ላይ ያሉ የመንግስት ሠራተኞችና የመንግስት የልማት ድርጅቶች የትም/ት፣ የሥራ ልምድና የመንጃ ፈቃድ ትክክለኛነት በማጣራት ሲቪል ሰርቪሱ ከዚህ ዓይነት ወንጀል መጽዳቱን ማረጋገጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በመቀጠልም የሠራተኛ ስምሪት፣ ቅጥር፣ ዝዉዉርና የደረጃ ዕድገት በትክክለኛ ማስረጃ መፈጸሙን በማረጋገጥ ውጤታማ የተልዕኮ አፈጻጸም እንዲኖር ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ለአንድ ሀገር እድገት የሰው ኃይል ልማት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዉ  እያንዳንዱ ሠራተኛ ለደረጃው የሚመጥን በቂ እውቀት መያዝ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ሰራተኛው የትምህርት ደረጃውንና የስራ ልምዱን የሚመጥን ቦታ ላይ ሲመደብ የሥራ ቅልጥፍናው እንዲጨምርና ዕቅዱ ግቡን እንዲመታ የሚያስችል በመሆኑ ለሀገር ዘላቂ እድገትም አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡ ስለሆነም የማጣራቱ ሥራ የሚሠራው  አዎንታዊ በሆነ የማስተካከያ መንገድና ሰዎችን በማይጎዳ ሁኔታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ቀኑን ስናከብር የሰዎችን መጥፎ ሥነ-ምግባር ወደ መልካም ለመመለስ ይቻላል የሚል አስተሳሰብ በማዳበር ነው ያሉት የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር መልካሙ ማዳ ይህን ማድረግ ሲያቅተን ግለሰቦች የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ውስጥ ተጠምደው እንደሚቀሩ ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎቻችንም ከማይወጡበት የሙስና አስተሳሰብ ውስጥ እንዳይዘፈቁ ከወዲሁ በመልካም ሥነ-ምግባር ማነጽ ይገባል ብለዋል፡፡

የውይይት ሰነዱን አስመልክቶ ከታዳሚዎች ጥያቄና አስተያየት እንዲሁም የዕለቱን ፕሮግራም ሙስናን የተመለከቱ ግጥሞች በተማሪዎች የቀረቡ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ የየካምፓሱ የሥራ ኃላፊዎች፣ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች በበዓሉ ታድመዋል፡፡