የ2010 ዓ.ም የ6 ወራት አፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ2010 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ጥር 10/2010 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ የስትራቴጂክ ዕ/ት/ግ/ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዝሙ ቀልቦ ባቀረቡት የ6 ወራት የአፈፃፀም ሪፖርት በትምህርት ጥራትና በመማር ማስተማር፣ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት፣ በመልካም አስተዳደርና በቢዝነስና ልማት ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ዝርዝርና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

በሪፖርቱ እንደተመለከተው የ2010 በጀት ዓመት ዕቅድ በውጤት ተኮር ሥርዓት ተዘጋጅቶ በየደረጃው ባሉ የሥራ ዘርፎች ከኃላፊዎች እስከ ፈፃሚ ድረስ የዕቅድ ውል ስምምነት መፈረሙ፣ የምርምር መረጃ ቋት ተቋቁሞ ስራ መጀመሩ፣ የትምህርት ጥራትን የበለጠ ለማጠናከር በበጀት ዓመቱ የዴሊቨሮሎጂ ጽንሰ ሀሳብ ሥልጠና ለመላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ መሰጠቱ እና የዴሊቨሮሎጂ ዩኒት መቋቋሙ እንዲሁም በእያንዳንዱ ት/ክፍል በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የ241 ተጨማሪ መምህራን ቅጥር መፈፀሙ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተጨማሪም ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በባህላዊ መድሃኒቶች አጠቃቀም ላይ ሀገር አቀፍ ሲምፖዚዬም መካሄዱ፣ ከሦስት የተለያዩ ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጥምረት የሚተገበር Research based education for livelihood improvements ፕሮጀክት ሥራ ለማስጀመር በቂ ዝግጅት መደረጉ፣ የተደራጁ ወቅታዊ ዜናዎችንና የዩኒቨርስቲውን በጎ ገጽታ የሚያስተዋወቁ ጠቃሚ መረጃዎች በመገናኛ ብዙሀን መሰራጨታቸው፣ በዩኒቨርሲቲው ከተቀጠሩ አዲስ መምህራን 91ንዱ የማስተማር ስነ-ዘዴ (Instructional skill) ስልጠና ማግኘታቸው፣ የዲጂታል ላይብረሪ እና የኢ-ሪሶርስ አገልግሎትን ለማሻሻል 6,672 ሶፍት ኮፒ መጽሐፍቶች (E-book & E-Journal)፣ የመመረቂያ እና የምርምር ጹሑፎች መሰባሰባቸውና 465‚000 Full Text Articles ወደ መረጃ ቋት (ኢንስቲትዩሽናል ሪፖዚተሪ/IR) ገብተው ለንባብ ዝግጁ መደረጋቸው  በመማር ማስተማር እና በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፎች ከተገኙ ስኬቶች መካከል ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው በውኃ ምህንድስና ዘርፍ የነበረውን ከፍተኛ አቅምና ዝና ወደ ነበረበት ማማ ለመመለስ የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳግም ራሱን ችሎ እንዲመሠረት መደረጉ፣ በየትምህርት ክፍሉ፣ በየኮሌጁና በኢንስቲትዩት ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የተማሪዎች ቅሬታና አቤቱታ ማስተናገጃ ሥርዓት መዘርጋቱ፣ በሣውላ ካምፓስ ከሦስት የዶርሚተሪ ሕንጻዎች ግንባታዎች ሁለቱ ተጠናቀው አግልግሎት መስጠት መጀመራቸውና ሦስተኛውም ህንፃ እየተጠናቀቀ መሆኑ፣ በግብርና ሣይንስ ኮሌጅ አንድ የከብቶች ህክምና መስጫ/ካትል ክራሽ (cattle-crash) ሕንፃ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ፣ በአባያ፣ ጫሞ እና ነጭ ሳር ካምፓሶች የግንባታ ሥራቸው የተጠናቀቁ ሕንፃዎች ጊዜያዊ ርክክብ ተደርጎ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው፣ የማናጅመንት ህንፃን ከጎርፍ ለመከላከል የሚያስችል የጋቢዮን ግንባታ ተጠናቆ ጊዜያዊ ርክክብ የተደረገ ሲሆን በተመረጡ በሶስት ቦታዎች (10‚000 ካ.ሜ) ላይ የተማሪዎች ማጥኛ ፓርክና የግቢ ዉበት ሥራዎችም  በተሻለ አፈፃፀም ተከናውነዋል፡፡

የግንባታ ሥራዎች ቁጥጥር በተለያዩ ሳይቶች በቋሚነት መካሄዱ፣ ከሥራ ባህሪያቸው አንጻር በትርፍ ሰዓት ጭምር ለሚሠሩ የሥራ ክፍሎች የትርፍ ሰዓት ክፍያን ማስፈቀድ መቻሉ፣ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የመፀዳጃ ቤቶች አጠቃቀም ሥርዓት እንዲጠናከርና አዳዲስ መፀዳጃ ቤቶችም እንዲገነቡ መደረጉ፣ ተጨማሪ የእግር ኳስ መጫወቻ ሥፍራዎች መዘጋጀታቸውና ክሊኒኮች የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሠጡ መሆኑ በአስተዳደራዊና በቢዝነስና ልማት ዘርፎች ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡

በአንፃሩ ደግሞ በመካከለኛና ከፍተኛ አመራር ቦታዎች የሴቶች ተሳትፎ ማነስ፣ የተሽከርካሪ እጥረት፣ የመብራት መቆራረጥ፣ የመምህራን እጥረት፣ የአገልግሎት ጨረታ በሚወጣበት ወቅት በቂ ተወዳዳሪ ያለመቅረብ፣ የማዕቀፍ ግዥዎች መዘግየት፣ በአንዳንድ የሥራ መደቦች ደረጃውን የሚመጥን ባለሙያ ያለመገኘት እና የመሳሰሉት በአፈፃፀም ወቅት የታዩ ችግሮች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

በ6ቱ ወራት የታቀዱ ተግባራት በአግባቡ መከናወናቸውን በመገምገም ዝቅተኛ አፈፃፀም በታየባቸው መስኮች በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ የዩኒቨርሲቲው ኘሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርን ትኩረት ሰጥቶ መስራት፣ የትምህርት ጥራትና መልካም አስተዳደር ፎረም ውይይቶችን እንደ ግብዓት በመውሰድ ከተማሪዎች፣ ከመምህራንና ከአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ጋር የተያያዙ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን ለማስተካከል አጠናክሮ መሥራት፣ የምርምር ውጤቶችን ማላመድና ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተጠቃሚው ማህበረሰብ ማሸጋገር፣ የገቢ ማመንጫ አማራጮችን በመጠቀም ገቢን ማሳደግ፣ የካፒታልና የመደበኛ በጀት አጠቃቀምን ማሻሻል፣  ሴቶች ወደ ምርምሩ ዘርፍ እንዲመጡ ልዩ ድጋፍና ክትትል ማድረግና በግማሽ ዓመቱ ዕቅድ አፈፃፀም ዝቅተኛ ውጤት የተመዘገበባቸውና ያልተፈፀሙ ተግባራትን በቀጣይ ግማሽ አመት በማካተት በትጋት መፈፀም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል፡፡

በአፈፃፀም ግምገማው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና አስተባባሪዎች ተገኝተዋል፡፡