“SAM-UP” ክበብ የተማሪዎችን ውጤታማነት ለማሳደግ እየሰራ ነው

የዩኒቨርሲቲውን ተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል በ2009 ዓ/ም በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ግቢ ተቋቁሞ ሥራውን የጀመረው የ“SAM-UP”- ‘Students’ Academic Mission –Upgrade’ (የተማሪዎች የትምህርት ተልዕኮ ማሻሻያ) ክበብ አበረታች ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

ክበቡ የላቀ ውጤት ከሚያስመዘግቡ ተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም ሌሎች ለመማር ማስተማር ሂደት አጋዥ ከሆኑ የትምህርትና የሥራ ክፍሎች ጋር በመተባበር ለሴት፣ ለአካል ጉዳተኛ፣ ልዩ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ክልሎች ለመጡ እና በትምህርታቸው አነስተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠትና ሌሎችም ለአካዳሚክ ሥራ አጋዥ የሆኑ ተግባራትን በማከናወን የተማሪዎች የትምህርት ተልእኮ እንዲሳካ እየሠራ መሆኑን የክበቡ መሥራችና ፕሬዝደንት ተማሪ ታመነ ታዬ ገልጿል፡፡

በክበቡ አማካኝነት በተጠናቀቀው መንፈቀ ዓመት ከ4000 በላይ ከ1ኛ-5ኛ ዓመት ከየትምህርት ክፍሉ በተመለመሉ ወንድ 58 እና ሴት 15 ተማሪዎች በድምሩ 73 ተማሪዎች እንዲሁም በ3 ሴትና በ6 ወንድ መደበኛ መምህራን የማጠናከሪያ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን ድጋፉን ካገኙት መካከል ከጋምቤላ እና ሌሎች ታዳጊ ክልሎች እንዲሁም ከደቡብ ሱዳን እና ሶማልያ የመጡ ተማሪዎች ተካተዋል፡፡ ሴት ተማሪዎች ከማጠናከሪያ ትምህርቱ በተጨማሪ በልዩ ሁኔታ በግልና በቡድን እንዲረዱም ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የኮምፒዩተር ላቦራቶሪዎች ለ24 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጡ የተደረገ ሲሆን ለመማር ማስተማር ሥራ አጋዥ ሶፍትዌሮች አጠቃቀምን አስመልክቶ ስልጠና በመስጠት እገዛ መደረጉን ተማሪ ታመነ ተናግሯል፡፡  የsoftware ስልጠናው እንደ Auto CAD፣ WaterCAD፣ Solidwork፣ StormCAD፣ Java፣ GIS፣ C++፣ Cropwatt፣ SAP እና ሌሎችን ያካተተ ነው ብሏል፡፡

በቀጣይ የማጠናከሪያ ትምህርትና የሶፍትዌር ስልጠና አሰጣጡን በየደረጃው ማስፋት፣ ለአካል ጉዳተኞች ለብቻ የማጠናከሪያ ትምህርት ማዘጋጀት፣ ከቤተ-መጽሐፍት ሰራተኞች ጋር በመሆን ተማሪ በብዛት የሚጠቀምባቸው መጽሐፍትን ለይቶ ለብቻ ካታሎግ ማዘጋጀት እና አዲስ የመጡ መጽሐፍት ካሉ ለተማሪዎች ማስተዋወቅ፣ ከቤተ-ሙከራ ረዳት መምህራን ጋር በመተባበር ተማሪዎቹ የቤተ-ሙከራ ስራውን እስኪረዱ ድረስ ቆይቶ ማሰራት፣ አንድ ለአምስት አደረጃጀት እንዲጠናከር ማገዝ፣ መምህራን ለክበቡ አስተዋፅኦ የሚያደርጉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ የፈጠራ ክህሎት ያላቸው ተማሪዎችን መመልመልና ክበቡን ወደ ፎረም የማሳደግ ተግባራት በትኩረት የሚከናወኑ ይሆናል፡፡

ተማሪ ታመነ በዩኒቨርሲቲው የተማሪ አደረጃጀቶችን አብቅቶ ግልፅ ተልዕኮ በመስጠት የበኩላቸውን እንዲወጡ ማድረግ ለመማር ማስተማር ሂደት መቀላጠፍና ለውጤታማነቱ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ጠቅሶ አስፈላጊ ግብኣቶች በበቂ መጠንና በወቅቱ ቀርበዉ ስራ ላይ እንዲውሉ የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ወሳኝነት ያለው መሆኑን ተናግሯል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻል ያሳዩ አደረጃጀቶች በግልጽ የታዩ ሲሆን የ“SAM-UP” ክበብ ጅምር እንቅስቃሴም ለዚህ ማሳያ በመሆኑ እንቅስቃሴው ተጠናክሮ ወደሚፈለገው ደረጃ እንዲደርስ በሁሉም አካላት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብሏል፡፡

የክበቡ አደረጃጀት ባሁኑ ሰዓት በሁሉም ካምፓሶች ተዋቅሮ የተጠናቀቀ ሲሆን በአባያና ጫሞ ካምፓሶች የማጠናከሪያ ትምህርት አሰጣጡ ከፋይናል ፈተና ዝግጅት ጋር ተጀምሯል፡፡ በ2ኛው መንፈቀ ዓመት በሁሉም ካምፓሶች የአገልግሎት አሰጣጡ በተጠናከረ ሁኔታ የሚቀጥል መሆኑ ተገልጿል፡፡