ለርዕሳነ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና ነባር መምህራን ስልጠና ተሰጠ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሣይንስ ትምህርት ቤት በጋሞ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ እና ሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ለሚገኙ የሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት 150 ርዕሳነ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና ነባር መምህራን በተግባራዊ ምርምር፣ በተግባር ትምህርት እና ድጋፍ አሰጣጥ/ሜንተር ሺፕ/ ከጥር 24-26/2010 ዓ/ም ለ3 ተከታታይ ቀናት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ትምህርት ቤት ዲን ዶ/ር ኢዮብ አየነው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ዩኒቨርሲቲው እንደ አንድ የትምህርት ተቋም በአካባቢው ባሉ ዞኖች የሚገኙ ጀማሪ መምህራንን ብቃት ለማሳደግ ነባር መ/ራንና የትምህርት ቤት አመራሮችን በማሰልጠን በስራቸው ላሉት መምራን ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ያደርጋል ብለዋል፡

እንደ ዲኑ ገለፃ በዩኒቨርሲቲው የተግባር ምርምር ትልቅ አፅንኦት ተሰጥቶት እየተሰራበት ሲሆን ይህ ስልጠናም መምህራን በአካባቢያቸው ያሉ ችግሮችን በምርምር በመለየት መፍትሄ እንዲያፈላልጉ የሚያደርግ ነው፡፡ አብዛኞቹ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ ምሩቃን መሠረታዊ የማስተማር ክህሎትን ሰልጥነው እንደማይወጡ የገለፁት ዶ/ር ኢዮብ የመማር ማስተማር ስራ በእውቀት ብቻ የሚተገበር ሳይሆን የማስተማር ስነ-ዘዴ ክህሎትም የሚያስፈልገው በመሆኑ ሰልጣኞቹ አዲስ የሚቀጠሩ መምህራንን በማለማመድ የተማሩትን ወደተግባር እንዲቀይሩ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል፡፡

በስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ትምህርት ቤት የፔዳጎጂካል ሣይንስ መ/ር ዶ/ር ቾምቤ አናጋው ስልጠናውን ሲሰጡ ጀማሪ መምህራን በ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ሲመደቡ ልምድ ያላቸው መ/ራን ኃላፊነትና ድጋፍ አሰጣጥ እንዲሁም ጀማሪ መምህራን ከተመደበላቸው አማካሪ ጋር ተግባብተው የሚሰሩበትን መንገድ አብራርተዋል፡፡ የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት በ2ኛ ደረጃ ት/ቤት የሚመደቡ መምህራን እንደመሆናቸው መጠን ሰልጣኞቹ ወደ ትምህርት ቤት ሲመለሱ ለመምህራን ስልጠናውን በመስጠት የተሻለ ውጤት እንዲመጣ አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው ዶ/ር ቾምቤ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ካለፉት 27 ዓመታት ጀምሮ በየደረጃው ባሉ እርከኖች ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋትና ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ በማድረግ ከትምህርት የሚገኘውን ትሩፋት ለመቋደስ በሚቻልበት ደረጃ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ስልጠናው የመምህራንን ሙያዊ ብቃት በመገንባት የትምህርት ጥራትን በየትምህርት ቤቱ ለማምጣት ያግዛልም ብለዋል፡፡

ሰልጣኞቹ በሰጡት አስተያየት በመማር ማስተማር ሂደት ጎልተው የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ በማውጣትና መፍትሄ በመፈለግ ስኬታማ የመማር ማስተማር ተግባርን ለማከናወን የሚያስችል በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልፀው ያገኙትን ክህሎት ወደየትምህርት ቤታቸው አውርደው ጀማሪ መምህራን በማስተማር ተግባርና በምርምር ዘርፍ እንዲበቁ የሚያግዟቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡