በሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት የኤች አይ ቪ/ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ቡድን በነጭ ሳር ካምፓስ ከሚገኙ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር በዜሮ ፕላንና ሪሶርስ ሴንተር ዓላማ፣ አስፈላጊነትና አተገባበር ላይ የካቲት 01/2010 ዓ/ም ውይይት አካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ቡድን ባለሙያ አቶ መርክነህ መኩሪያ  እንደተናገሩት ዜሮ ፕላን ፆታዊ ጥቃት፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ ጥንቃቄ የጎደለው ውርጃ፣ ኤች አይ ቪ /ኤድስ እንዲሁም መጠነ ማቋረጥ፣ መልሶ ቅበላ፣ መባረርና የመሳሰሉ በሴት ተማሪዎች ላይ የሚከሰቱ የስነ-ተዋልዶ ጤና ችግሮችንና መዘዞችን ለመቀነስ  ብሎም  ወደ  ዜሮ  ለማምጣት  ለሴት  ተማሪዎች  ብቻ የሚታቀድና  የሚከናወን ነው፡፡ ሴት ተማሪዎች ያልተፈለገ እርግዝና እንዳይከሰትና ቢከሰት ሊወሰድ ስለሚገባ እርምጃ መረጃ የሚለዋወጡበት ከመሆኑም ባሻገር በተለያዩ ሱሶች ውስጥ ያሉ ሴቶች የምክር አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ጥሩ ውጤት ያላቸው ሴት ተማሪዎች ደከም ያሉ ተማሪዎችን የሚያስጠኑ ሲሆን ስለትምህርታቸውም ይወያዩበታል፡፡ አገልግሎቱ በነጭ ሳር፣ በጫሞና በዋናው ግቢ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን በቀጣይ በሌሎች ካምፓሶችም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አቶ መርክነህ ተናግረዋል፡፡

አቶ መርክነህ በማብራሪያቸው የመረጃ ማዕከሉ/ሪሶርስ ሴንተር/ ሴት ተማሪዎች ስለ ስነ-ተዋልዶ ጤናና ኤች አይ ቪ/ኤድስ የተለያዩ የህትመት መረጃ የሚያገኙበት፣ በኮምፒዩተር የታገዘ የስነ-ተዋልዶ ጤና ትምህርት /CSE/የሚማሩበትና እየተዝናኑ ግቢ ውስጥ የሚቆዩበት ነው ብለዋል፡፡ የኮምፒዩተር ችግር ያለባቸው ሴት ተማሪዎች መመረቂያ ጽሑፋቸውን በማዕከሉ የሚያዘጋጁ ሲሆን የኮምፒዩተር ክህሎታቸውንም ያሳድጉበታል፡፡

የጤና ሣይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ከኤች አይ ቪ/ኤድስና ስነ-ተዋልዶ ጋር ተያይዞ በተለይ ሴት ተማሪዎች ካልተፈለገ እርግዝና ራሳቸውን የሚጠብቁበትና ከተከሰተም መፍትሔ የሚያገኙበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡