ዩኒቨርሲቲው ከቆዳ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ከፌዴራል የቆዳ ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ አዲስ አበባ በሚገኘው የኢንስቲትዩቱ ቅጥር ግቢ የካቲት 5/2010 ዓ/ም ተፈራርሟል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ከዚህ ቀደም ተማሪዎች ኢንደስትሪው በሚፈልገው መልኩ የሰለጠኑ ባለመሆናቸው ለቅጥርም ሆነ ወደ ሥራ ለመሰማራት ሲቸገሩ መቆየታቸውን የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ገልፀዋል፡፡ ይህ ትስስር በሁለቱ መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት በጋራ በመናበብ መስራቱ አስፈላጊ በመሆኑና አንዱ ለሌላው ግብአት ሆኖ እንዲያገለግል የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ የሚመረቁ ተማሪዎች ኢንደስትሪው በሚፈልገው መልክ ሰልጥነው ወደ ስራ በሚሰማሩበት ወቅት በሙያው ይበልጥ ተክነው እንዲወጡ የሚያግዝ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ዩኒቨርሲቲው ለሀገሪቱ እድገት ወሳኝ የሆነውን የሠለጠነ የሰው ኃይል በጥራት ለማብቃትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት እየሰራ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለመክፈት ባቀደው የቆዳ ቴክኖሎጂ ትምህርት ክፍል የሚያስተምራቸውን ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ እና በተግባር ትምህርት በማነጽ ከኢንደስትሪው ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲኖራቸው ለማድረግ ትስስሩ ወሳኝ ነው፡፡

የቆዳ ልማት ኢንስቲትዩት ለዘርፉ ውጤታማነት የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠር በማገዝ፣ በምርምርና ስርጸት እንዲሁም በምርት ጥራት ደረጃና በማርኬቲንግ አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ለዘርፉ እድገት የሚሠራ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ም/ጀኔራል ዳይሬክተር አቶ መሃመድ ሁሴን ገልጸዋል፡፡ ሀገሪቱ ከቆዳ ሀብቷ ከፍተኛ ተጠቃሚ እንድትሆን የማድረግ ተልዕኮን ይዞ እንደሚንቀሳቀስም ተናግረዋል፡፡

ሁለቱም ድርጅቶች ለሀገሪቱ እድገት ወሳኝ የሆነውን የሰው ኃይል በጥራት ለማፍራትና በቆዳው ዘርፍ ሀገሪቱ የተሸለ ጥቅም እንድታገኝ ለማስቻል ካላቸው ቁርጠኝነት በመነሳት ጥናትና ምርምር በጋራ ለማካሄድ፣ የማማከርና ስልጠና ሥራ ለመስራት እንዲሁም የጥናትና ምርምር ሥፍራዎችን፣ ላቦራቶሪዎችን፣ ዎርክ ሾፖችንና የመሳሰሉ ቁሳዊ ሀብቶችን እና ያላቸውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በጋራ ለመጠቀም ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ በቅርቡም ለቴክኒክ ረዳቶች ስልጠና ለመስጠት የታቀደ ሲሆን በመቀጠልም ወደ ሥርዓተ-ትምህርት ቀረፃና ሌሎች ለትምህርት ክፍሉ ሥራ መጀመር ቀዳሚ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡