ዩኒቨርሲቲው በህግ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ውጤታማ መሆኑን ገለጸ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ2007 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የህግ ተመራቂ ተማሪዎችን የመውጫ ፈተና ያስፈተነ ሲሆን በመጀመሪያው ፈተና የተወሰኑ ተፈታኞች ማለፍ ባይችሉም በተከታዮቹ 2 ዓመታት ግን ሙሉ በሙሉ ስኬታማ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

ስኬቱን ለማረጋገጥ ለተማሪዎች ተጨማሪ የማጠናከሪያ ትምህርትና የተለያዩ ድጋፎች የተደረገላቸው መሆኑን የህግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ ደርሶልኝ የኔአባት ተናግረዋል፡፡ ፈተናው ተማሪዎች በቆይታቸው ያካበቱትን የህግ ትምህርት መሠረታዊ ጉዳዮች መገንዘባቸውን ለመፈተሽ የሚዘጋጅ በመሆኑ በቂ ዝግጅት ከተደረገበት የታለመውን ውጤት ማግኘት እንደሚቻል የጠቆሙት ዲኑ የትምህርት ቤቱን ውጤታማነት ለማስቀጠል አጠናክረን እንሠራለን ብለዋል፡፡ ጥራት ያለው ባለሙያ ከማፍራት አንፃር ተሞክሮው በሌሎችም የትምህርት ዘርፎች ተግባራዊ ቢደረግ መልካም መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ለህግ ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና መኖሩ የፍትህ ሥርዓቱ ውጤታማ እንዲሆንና እንዲስተካከል፣ የሰላምና ዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንዲጠናከር ብሎም ሙስናን በመከላከልና ሥነ-ምግባር ያለው ባለሙያ በማፍራት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው አቶ ደርሶልኝ ተናግረዋል፡፡ ፈተናው ከተጀመረ በኋላ በዘርፉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ የማስተማሪያ መፅሃፍትና ሞጁሎች የተዘጋጁ በመሆኑ ተማሪዎችን አብቅቶ በማሳለፍ ረገድ የህግ ትምህርት ቤቶች የብቃት ደረጃቸውን እንዲለኩ የሚያደርግ ነው፡፡

የህግ ትምህርት ቤት መምህር ማሞ ገንጮ እንደገለፁት ፈተናው ተማሪዎች ለ5 ዓመታት የተማሩትን እንደገና እንዲከልሱ የሚያደርግና የህግ ትምህርት መሠረታዊ ጉዳዮችን በትክክል መረዳታቸውን የሚፈትሽ ከመሆኑም ባሻገር ዋና ዋና የህግ ጉዳዮችም የሚዳሰሱበት ነው፡፡

የ5ኛ ዓመት የህግ ተማሪ ደሳለኝ ዘማርያም በሰጠው አስተያየት የመውጫ ፈተናው የተማሩትን በአግባቡ መረዳታቸውን ማረጋገጫና የዕውቀት አድማስን የሚያሰፋ በመሆኑ ከወዲሁ የተለያዩ መፅሃፍትን በማንበብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ የሚያነቡት ለፈተና ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡን የሚጠቅም ዕውቀት ይዞ ለመውጣት እንደሆነም ተናግሯል፡፡

የህግ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና በሀገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ የሚዘጋጅ ሲሆን ፈታኞቹ ከዩኒቨርሲቲው ሌሎች የትምህርት ክፍሎች የተወጣጡ ይሆናል፡፡ የኤጀንሲው ሱፐርቫይዘሮችም የፈተናውን ሂደት ይከታተላሉ፡፡